Fana: At a Speed of Life!

15 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ በተጭበረበረ መንገድ እንዲወሰድ አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቢሻን ጉራቻ ከተማ የሊዝ ክፍያ ሳይከፈል 15 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ በተጭበረበረ መንገድ እንዲወሰድ አድርገዋል የተባሉ የቀድሞ የከተማው የገቢዎች ፅህፈት ቤት ኃላፊ እና ባለሙያን ጨምሮ 3 ተከሳሾች ከ7 እስከ 18 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የምዕራብ አሪሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ 1ኛ የቢሻን ጉራቻ ከተማ ባለሀብት ግለሰብ ነው የተባለ መሀመድ ሁሴን፣ 2ኛ ተከሳሽ የቢሻን ጉራቻ አስተዳደር የገቢ ሰብሳቢ ባለሙያ አማንኤል ሰይፉ እና 3ኛ ተከሳሽ የከተማው አስተዳደር የቀድሞ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ጫላ ለታ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1ሀ እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9/2 ተላልፈዋል በማለት በዋና ወንጀል አድራጊነት 3 ተደራራቢ የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በዚህ ክስ ላይ እንደተመላከተው ባለሀብት ነው የተባለው 1ኛ ተከሳሽ በቢሻን ጉራቻ ከተማ ውስጥ 15 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ እንዲሰጠው በጠየቀው ጥያቄ መነሻ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት በቦርድ አማካኝነት የሊዝ ክፍያ ከፍሎ እንዲወስድ በተሰጠ ፍቃድ መነሻ 10 ከመቶ ማለትም 2ሚሊየን 250 ሺህ ብር የሊዝ ክፍያ እንዲከፍል ተወስኖ እንደነበር በክሱ ተመላክቷል።

በዚህ የሊዝ ውሳኔ መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር የሊዝ ክፍያውን እንደከፈለ በማስመሰል ባለሀብቱ የሊዝ ገንዘቡን ገቢ ሳያደርግ ነሃሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በ2ኛ ተከሳሽ ባለሀብቱ ክፍያ እንደተፈጸመ አድርጎ ደረሰኝ ቆርጦ መስጠቱ በክሱ ተዘርዝሯል።

በዚህ መልኩ ክፍያ ሳይፈጸም ደረሰኝ ከተቆረጠ በኋላ የቢሻን ጉራቻ ከተማ ገቢዎች

ፅህፈት ቤት ኃላፊ የነበረው 3ኛ ተከሳሽ ደግሞ የሊዝ ክፍያ ፈጽሟል በማለት ለ1ኛ ተከሳሽ የካርታ ፕላን እንዲሰራለት በማስደረግ በነሀሴ 18 ቀን 2013ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ ካርታ እንዲወስድ መደረጉ በቀረበ በሁለት ክስ ላይ ተጠቅሷል።

3ኛ ክስ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን÷ በአኳን ባንቡ ፕሮጀክት ፒኤልሲ ስም ያልተከፈለ የካርታ ቀብድ ቼክ የተሰጠ በማስመሰል 1ኛ ተከሳሽ በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ባለው ሒሳብ ውስጥ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው በተለያዩ መጠኖች አጠቃላይ 2 ሚሊየን 250 ሺህ ብር 3 ደረቅ ቼኮችን ጽፎ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም ለ3 ኛ ተከሳሽ ሰጥቷል የተባለ ሲሆን÷በዚህም አንቀጽ 693/1 በመተላለፍ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ደረቅ ቼክ መጻፍ ወንጀል ተከሷል።

ቀኑ ያለፈበት በ1ኛ ተከሳሽ ተጽፎ ተቆርጦ የተሰጠ የ 2ሚሊየን 250 ሺህ ብር መጠን ያለው 3 ቼኮች በ3ኛ ተከሳሽ በገቢዎች ፅህፈት ቤት ኃላፊ እጅ ላይ ከሁለት ወራት በኋላ በህዳር ወር 2015 ዓ.ም መገኘቱም በክሱ ተዘርዝሯል።

አጠቃላይ 3 ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አሪሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸው እና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ ክደው ተከራክረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ዐቃቢህግ የሰነድ ማስረጃን እና ከአራት በላይ የሰው ምስክሮችን አቅርቦ ነሃሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በችሎት የምስክር ቃል አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቢህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ ሳይከላከሉ በመቅረታቸው ምክንያት በመጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ተከሳሾችን የቤተሰብ አስተዳዳሪና መሆናቸውን ጠቅሰው ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት እና ዐቃቢህግን ቅጣቱ ከብዶ እንዲጣልለት ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት በመያዝ ፍርድ ቤቱ 1ኛ ጥፋተኛ በተባለበት አንቀጽ በ18 አመት ጽኑ እስራትና በ15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

የገቢ ሰብሳቢ ባለሙያ የሆነውን 2ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ7 አመት ጽኑ እስራትና በ5ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን÷ የቢሻን ጉራቻ ገቢዎች ቢሮ የቀድሞ ኃላፊን የነበረውን 3ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ9 አመት ጽኑ እስራትና 6 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.