Fana: At a Speed of Life!

“ሰላም እንደ ጦርነት ነው፤ ጀግንነት ይፈልጋል፤ ከጦርነት ያልተናነሰ ሥራ፣ ድካም ይጠይቃል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም ከእኛ ይቅር በሚል አብረን እንትጋ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡

ሰላምን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባነሱት ሃሳብም፥ ሰላም አንጻራዊ መሆኑን በመጥቀስ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም እንደ መንግስት እና እንደህዝብ በአንድነት መስራት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ የተፈጠረው ግጭትን የማቆም ውሳኔን ተከትሎ የመጣውን የሰላም ሁኔታ እንደአብነት አንስተዋል፡፡

ሆኖም የድህረ ግጭት ጫና እንዳለ ጠቅሰው ፥ ግጭቱ በዜጎች ላይ ያሳደረው ጫና በቀላሉ የሚሽር እንዳልሆነም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም የሰላም አየር ተንፍሰናል ብሎ መረጋጋት የሚያስችል እንዳልሆነም አብራርተዋል፡፡

ግጭት ቀስቃሽ ኃይሎችም ሀገር በመረጋጋት ሰላሟ እንዲረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የሰላም ማጣቶች ዋነኛ ምክንያቶቸ ናቸውም ብለዋል፡፡

“አሁን የሚያስፈልግን ሰላምና ነው እንጂ መገዳደልና መጠላላት እይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት ሰላም ፈላጊ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የሚፈፀማቸውን ተግባራት እንደአብነት አንስተዋል፡፡

ከህዝብ ጋር በሚደረገው ውይይትም ለሰላም ያለውን ጉጉት ለማየት እንደተቻለ አንስተው ፥ ሰላምን ማምጣት ጀግንነት ይፈልጋልና ለዚህም ብዙ ጥረቶች መደረጋቸው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡

ሰላም ከጦርነት ያልተናነሰ ትጋት ይጠይቃል በማለት፥ በተለይም አዎንታዊ ሰላም በኃይል ብቻ የሚረጋገጥ አይደልም ሲሉም ነው ያነሱት፡፡

“ለሰላም ከእኛ ይቅር በሚል አብረን እንተጋ” በማለት አደራ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚህ መሳካት መትጋት አለበት ብለዋል፡፡

ሰላም ለማምጣት የሚያስፈልጉ የንግግር፣ የምክክር፣ የመተማመን ስራዎች በስፋት መጀመራቸውን ጠቅሰው ፥ እነዚህ ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘውም ስለሚዲያ ባነሱት ሃሳብ ሚዲያ መርጦ መስማት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የሚዲያ ነጻነት እስከምን ድረስ ነው ለሚለው ሃሳብ ማብራሪያ ሲሰጡም የሚዲያ ነጻነትን ችግሮችን ለማቃለልና ለመልካም ነገር መጠቀም ማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሚዲያዎች ሚና ማስተማር መሆን ሲገባው ወደጥፋት እየሄደ ያለውን ግጭት ቀስቃሽነት የብሮድካስት ባለስልጣን ህግ የማስከበር ስራ መስራት ይኖርበታልም ነው ያሉት፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.