Fana: At a Speed of Life!

ከለውጡ በኋላ የተገኘውን ድልና ስኬት ለማስቀጠል ያለመ የድጋፍ ሰልፍ ነገ በኦሮሚያ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከለውጡ በኋላ የተገኘውን ድልና ስኬት ለማስቀጠል ያለመ የድጋፍ ሰልፍ ነገ በመላው ኦሮሚያ ክልል እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል ነገ የሚካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ አስመልክቶ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ እንደገለጹት÷ የድጋፍ ሰልፉ የሚካሄደው ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ወዲህ በክልሉ የተመዘገቡ ድልና ስኬቶችን ጠብቆ ለማስቀጠል ነው።

ከለውጡ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማሕበራዊና በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ስለሆነም ነገ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ ህዝቡ ድልና ስኬቶችን ለማስቀጠል ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል ነው ያሉት።

በድጋፍ ሰልፉ በእነዚህ የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙና ወደ ፊትም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአብሮነትና በወንድማማችነት ለመሻገር ቃል የሚገባበት መሆኑንም አስረድተዋል።

ሰላማዊ ሰልፉን በተሳካ መንገድ ለማካሄድ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ ማጠናቀቁን በመግለጽ የክልሉ ሕዝብም የሰልፉ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የድጋፍ ሰልፉን ለማስተባበር ወጣቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና የጸጥታ አካላትም አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው የድጋፍ ሰልፉ ነገ ከጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምርም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.