Fana: At a Speed of Life!

መንግስትን ታክስና ቀረጥ በማሳጣት በሙስና ወንጀል የተጠረጠረው የጉምሩክ ሰራተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድ ዕቃ ባልተፈቀደ ቦታ እንዲራገፍ በማድረግ መንግስትን ታክስና ቀረጥ በማሳጣት በሙስና ወንጀል የተጠረጠረው የጉምሩክ ሰራተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡

ከጅቡቲ በኢትዮጵያ አድርጎ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚወጣ በሁለት ኮንቴነር የተጫነ የንግድ ዕቃ ደቡብ ሱዳን ሳይደርስ እንዲራገፍ በማድረግ መንግስትን ታክስና ቀረጥ በማሳጣት የሙስና ወንጀል ተጥርጥሮ ነው ግለሰቡ ፍርድ ቤት የቀረበው፡፡

ተጠርጣሪ ኢንስፔክተር ኡስማን ጣሃ በጅማ ጉምሩክ የመተሃር ቡርቤ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ ሆኖ እየሰራ በነበረበት ወቅት÷ ከጅቡቲ ተነስቶ የኢትዮጵያን ግዛት አቋርጦ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚወጣ የኦሞ ዱቄት ሳሙና ምርቶች እና ሌሎችም የንግድ ዕቃዎችን  ደቡብ ሱዳን ሳይደርስ የወጣ ለማስመሰል የፈታሾችን ፊርማ አስመስሎ ፈርሟል በማለት ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስረድቷል።

 

በዚህ መሰረት የንግድ ዕቃዎቹ ደቡብ ሱዳን ሳይደርሱ በ2014 ዓ.ም መጨረሻ አገር ውስጥ እንዲራገፉ በማድረግ መንግስት ከቀረጥና ታክስ ሊያገኝ የሚገባውን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ በማሳጣት የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ ነው ምርመራ እየተከናወነበት የሚገኘው።

በተጀመረ የምርመራ ስራ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡንና ሁለት የሰው ምስክር ቃል መቀበሉን ለጊዜ ቀጠሮ ያሳወቀው ፖሊስ ቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመቀበልና ተጨማሪ ማስረጃ ለመሰብሰብ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በበኩሉ  ነዋሪነቱ በጋምቤላ ከተማ መሆኑን እና በአሁን ወቅት የጤና መታወክ እንዳጋጠመው ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲያስከብርለት ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጣ ቀሪ ምስክሮችን ሊያባብልና ማስረጃ ሊያሸሽብኝ ይችላል ሲል ስጋቱን በመግለጽ÷ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ተከራክሯል።

የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊነትን በማመን ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን ውስጥ የሰባት ቀን የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.