Fana: At a Speed of Life!

ሩዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተገበያየ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩዝ ምርት ማገበያየቱን አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ በ2015 በጀት ዓመት ወደ ግብይት ሥርዓቱ ካካተታቸው የግብርና ምርቶች መካከል አንዱ የሆነው ሩዝ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በኤሌክትሮኒክስ የግብይት መድረክ መገበያየቱ ተገልጿል፡፡

በዚህ ግብይትም ቡሬ ቅርንጫፍ የገባ ደረጃ ሦስት ሩዝ በኩንታል 6 ሺህ 400 ብር የተገበያየ ሲሆን÷ በዕለቱም 60 ኩንታል ሩዝ በ 383 ሺህ 232 ብር መሸጥ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

የሩዝ ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓት መግባት የአምራቾች ተጠቃሚነትን በማሳደግ ለአምራቾች እና ለነጋዴዎች የገበያ መረጃን በበቂ ሁኔታ ለማሰራጨት፣ ወደ ውጭ የሚላከውን የምርት መጠን ለማሳደግ እና አምራችና ላኪውን በማገናኘት የተሳለጠ ግብይት መፍጠር እንደሚያስችልም ተጠቅሷል፡፡

አሁን ላይ ሩዝ በስፋት የሚመረተው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ትግራይ ክልሎች መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት ሥርዓቱን አጠናክሮ በመቀጠል በ2015 በጀት ዓመት አምስት የምርት አይነቶችን ወደ ግብይት ሥርዓት ማስገባቱን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.