Fana: At a Speed of Life!

ጆ ባይደን በቀጣዩ ምርጫ በድጋሚ እንደሚወዳደሩ ይፋ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ80 ዓመቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፈረንጆቹ 2024 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ እንደሚወዳደሩ ይፋ አደረጉ።

ከዴሞክራቶች ወገን ይሄ ነው የሚባል ጉምቱ ተፎካካሪ እንደሌለባቸው የተነገረ ሲሆን፥ በሪፐብሊካን ላይ ታሪካዊ ይሆናል የተባለለትን የምረጡኝ ዘመቻ ለማጧጧፍ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ብሉምበርግ የተሰኘው የአሜሪካ የዜና ምንጭ ዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን፥ “ዕድሜ ቁጥር ነው አያሳስባችሁ በድጋሚ ቢሮ እንድረከብ እና የጀመርኩትን ሥራ እንዳጠናቅቅ ምርጫችሁን በምትሰጡኝ ድምፅ ታረጋግጡልኝ ዘንድ እማፀናለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ዛሬ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የአሜሪካ ሴቶች ፅንስ የማቋረጥ መብታቸው እንዲከበር የጀመርኩትን ሥራ አጠናቅቅ ዘንድ ጉዳዩን አጥብቀው የሚቃወሙትን ፅንፈኛ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሰዎች እንዳሸንፍ የሚያስችለኝን የምርጫ ድምፅ ለኔ የመሥጠት ሥራ ይቀራችኋልም ብለዋል፡፡

በፈረንጆቹ ዕለተ ረቡዕ፣ ጥር 20 ፣ 2021 ላይ ዴሞክራቶችን ወክለው ሪፐብሊካኑን ዶናልድ ትራምፕ በማሸነፍ 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት የ80 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ በሙሉ ሥማቸው ጆሴፍ ሮቢኔት ባይደን ጁኒየር በድጋሚ ከተመረጡ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ማብቂያቸው ላይ 86 ዓመታቸውን ይደፍናሉ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.