Fana: At a Speed of Life!

ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ ቀንሷል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ መቀነሱን ባንኩ አስታወቀ፡፡

ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚመረተው ወርቅ በአግባቡ እየደረሰኝ አይደለም ብሏል ባንኩ፡፡

በ2015ዓ.ም 10 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለመግዛት መታቀዱን የባንኩ ምክትል ገዥ እና ዋና ኢኮኖሚስት ፍቃዱ ድጋፌ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 2 ሺህ 684 ኪሎ ግራም ወርቅ መግዛት መቻሉን ጠቅሰው÷ ይህም ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 62 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ንግዱ ፈተና መሆኑን ገልጸው ሁሉም ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

ባንኩ 35 በመቶ ጭማሪ አድርጎ በመግዛት ሕጋዊ ንግዱን ለማበረታት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው÷ የወርቅ ምርት እንዲቀንስ ያደረገው በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር ሳይሆን የኮንትሮባንድ ንግድ ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ክልሎች የሚሰጡትን ፈቃድ በአግባቡ ቁጥጥር አለማድረጋቸውን አመላክተው÷ በሕገ ወጥ ንግዱ የተሰማሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይ ወርቅን ጨምሮ በዋና ዋና የማዕድን ሃብቶች ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍም አዲስ የአሠራር አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ነው ያመላከቱት፡፡

በመሳፍንት እያዩ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.