Fana: At a Speed of Life!

ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ስጋትነቱ ቢያበቃም አሁንም ጥንቃቄ ያሻል ሲል ጤና ሚኒስቴር አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑ ቢነሳም አሁንም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች በሳርስ እና በኮቪድ-2 እንደሚያዙ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በዚህ ሳቢያ በርካቶች ለህልፈት እንደሚዳረጉ ጠቅሶ፥ አዲስ የበሽታው ዝርያ ሊከሰት የሚችልበት ስጋት እንዳለም አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንረጆቹ ጥር 30 ቀን 2020 ኮቪድ 19ኝን ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት እንደሆነ መፈረጁን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት እንደሀገር የመንግስት፣ የአጋር፣ ባለድርሻ አካላትና የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ በቀጣይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ጥረትን ለአዳዲስ ሁነቶች የዝግጁነትና ምላሽ አቅም ከማዳበር ስራ ጋር የማጣመር ስትራቴጂን ትከተላለችም ነው ያለው።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል የተገኘውን ሀገራዊ አቅም ማስቀጠልና ወደፊት ሊከሰቱ ለሚችሉ የጤና ችግሮችን የማዳበር ስራ ይሰራል ብሏል።

የኮቪድ-19 ክትባትን ከመደበኛ የክትባት መርሐ-ግብሮች ጋር ማቀናጀት እንዲሁም የኮቪድ-19 ምላሽ ትግበራንም ከመደበኛ የጤና ፕሮግራሞች ጋር አቀናጅቶ እንደሚሰራም ነው የገለጸው።

የህክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር፣ ተከታታይነት ያለው የማህበረሰብ ተሳትፎንና ግንዛቤን የማሳደግ ስራ እንደሚሰራም ጠቅሷል።

በተጨማሪም ከአፍሪካ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ከዓለም አቀፍ አካላት ጋር በመተባበር አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የህብረተሰብ ጤና ደህንነት አጀንዳዎች እንዲሁም በወረርሽኝ መከላከል፣ ዝግጁነትና ምላሽ አሰጣጥ ላይ መስራት ቀጣይ አቅጣጫዎች መሆናቸውን አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.