Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብን ገንብቶ ማጠናነቅ ለኢትዮጵያ የልማት ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ መሆኑ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የልማት ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ መሆኑን በአባይ ጉዳይ ብዙ ጥናት ያደረጉ እና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ገለፁ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ከኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ልኡክ አባል አቶ ዘሪሁን አበበ አባይ ከኢትዮጵያ አንጻር ሲታይ ከመልማትም አልፎ የህልውና ጉዳይ ይሆናል ይላሉ።

የሀገሪቱ ዋነኛ ሃብት የገጸ ምድር ውሃ መሆኑን ገልፀው በዓመት 112 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሃብት አላት ነው ያሉት።

ከዚህ ውስጥ 72 በመቶውን የሚሸፍነው የአባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ እና አኮቦ ወንዞችን የያዘው የአባይ ተፋሰስ መሆኑን አንስተዋል። በሃገሪቱ ካሉ 9 ክልሎችም ስድስቱ በዚሁ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ ከ45 እስከ 50 ሚሊዮን ህዝብ በቀጥታ ኑሮው በዚህ ተፋሰስ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።

ይህም ተፋሰሱ የሀገሪቱ ህልውና መሆኑን ያመላክታል ባይ ናቸው።

በዚህ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብም በሀገሪቱ ያለውን የጨለማ ኑሮ ወደ ብርሃን የመቀየር ስራ የሚመሰረትበት ፕሮጀክት ሲሆን፥ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ የኤሌክትሪክ ሃይል እየናፈቀ ያለው ህዝብ ብዛት መሆኑ ነው የተገለፀው።

ነገር ግን መሰል ድንበር ተሸጋሪ ወንዞች የአንድ ሀገር ብቻ ህልውና ሳይሆኑ የአስራአንዱም ሀገራት ነው።

ይህ የአባይ ተፋሰስ በተለያየ ምክንያት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት እንዳይጠቀሙበት ሲደረግ ቢቆይም ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ መገንባት ጀምራለች።

ይህን ያህል ጠቀሜታ ያለው ግድብ በተለይም በግብጾች ዘንድ እየታሰብ ያለው የቅንጦት እና ልዕልናን ለማረጋገጥ እንደሚገነባ ተደርጎ ነው ያሉትአቶ ዘሪሁን፥ ይህ ብዙ መነሻዎች ቢኖሩትም ግድቡ ግን ያለምንም ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምህንድስና ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ድግሪ ተማሪ የሆነችውና በአባይ ዙሪያ ጥናት እያደረገች ያለችው መቅደላዊት መሳይ በበኩሏ ተፋሰሱና እየተገነባ ያለው ግድብም የሀገሪቱ ህልውና ከመሆን ባለፈ የመንግስታቱ ድርጅት ያወጣው 17 የዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው ብላለች።

በአጠቃላይም አባይ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ እና በትብብር መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

 

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.