Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ 10 ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ 10 ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው።

 

መድረኩ የተጀመረው በቅርቡ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡት ለፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባል ለአቶ ግርማ የሺጥላ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነው።

 

በውይይቱ ላይ የሁሉም ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊዎች  የተገኙ ሲሆን ባለፉት 10 ወራት ብልፅግና ፓርቲ ከላይኛው እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ለመፈፀም ያቀዳቸው ተግባራት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በመገምገም ላይ ነው።

 

በተጨማሪም እንደ ፓርቲ የተያዙ እቅዶች በበጀት አመቱ መግቢያ ላይ በተያዘላቸው እቅድ መሰረት ተፈፃሚ ይሆኑ ዘንድ ግባቸውን ያልመቱ እቅዶችም በቀሪ ጊዜ ሊጠናቀቁ በሚችሉበት ሁኔታ ዙሪያ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓርቲው መረጃ ያመላክታል።

 

በውይይቱ መክፈቻ ላይ ባለፉት 10 ወራት በሁሉም ዘርፎች ውስጥ የተሰሩ ስራዎች አጠቃላይ ሪፖርት በገለፃ መልክ የቀረበ ሲሆን ለግምገማ ክፍት እንዲሆን ለተሳታፊዎች ቀርቧል።

 

በተለይም የፓርቲው ሁለንተናዊ የፖለቲካ፣ የኮሙኒኬሽን፣ የአደረጃጀት ፓርቲያዊ አቅምን ሊያዳብሩ የሚችሉ ተግባራት ባለፉት 10 ወራት በምን ያህል ደረጃ በተሳካ ሁኔታ እንደተፈፀሙ የግምገማው ይዘት በጥልቅ ይዳሰሳሉ ተብሏል።

 

ከ10 ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በተጨማሪም የመድረኩ ቀጣይ ትኩረት የ2016 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች ምን እንደሚመስሉ የሚዳሰሱ ሲሆን በፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፃ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በመጭው ክረምት ህብረተሰቡን እና መላው የብልፅግና ፓርቲ አባላት፣ አመራርና ደጋፊዎችን በማሳተፍ በሚሰሩ ሰፊ የንቅናቄ ስራዎች ዙሪያ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎም ይጠበቃል።

 

በተጨማሪም በግብርና፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ ያተኮሩ እንቅስቃሴዎች በምን መልኩ መፈፀም እንደሚገባቸው ምክክር ይደረጋል ነው የተባለው።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.