Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል ያለውን ግንኙነት በአዳዲስ መስኮች ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በአዳዲስ መስኮች ማሳደግ እንደሚገባ በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰይድ ሙሃመድ ገለጹ።

በኩዌት የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሰይድ ሙሃመድ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሳሌም አብደላህ አል-ጀብር አል-ሳባህ አቅርበዋል።

በዚህ ወቅት በነበራቸው ውይይትም አምባሳደር ሰይድ÷በኢትዮጵያ እና በኩዌት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በአዳዲስ መስኮች ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኩዌት በሚኖራቸው ቆይታም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር አንደሚሰሩና ለዚህም የኩዌት መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሳሌም አብደላህ አል-ጀብር አል-ሳባህ በበኩላቸው÷ ኩዌት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና ባለ-ብዙ ወገን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አሰታውቀዋል።

አምባሳደር ሰይድ በኩዌት በሚኖራቸው ቆይታ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ለሚሰሩት ስራ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

አምባሳደሩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተላከ መልዕክት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውንም  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.