Fana: At a Speed of Life!

ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በደላሎችና በመንግስት አካላት ጭምር እየተዘወረ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በደላሎችና ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የመንግስት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንደሚከናወን ፋና ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ምርመራ አረጋግጧል፡፡

ጣቢያችን ባደረገው ምርመራ ሀሰተኛ ሰነዶች እና ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገራት የተዘረጉ መረቦች ብዙዎችን ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ እያደረጉ ነው፡፡

በአዲሱ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መሰረት ዜጎች ወደ ውጭ ሀገራት ሲሄዱ መውሰድ ያለባቸው ስልጠናዎችና ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ቢኖሩም ገንዘብ በመክፈል ሀሰተኛ ማስረጃዎች እንደሚዘጋጁም በምርመራው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለዚህ ህገወጥ ስራቸውም ከ30 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር እንደሚጠይቁ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

ህገወጥ ተጓዦችም ስለሚሄዱበት ሀገርም ይሁን ስለሚሰሩት ስራ በቂ እውቀቱ የሌላቸው እንደሆነ ነው ለማረጋገጥ የተቻለው፡፡

ከዚህ ጋር በተገናኘ ገና በአፍላነት እድሜ የምትገኘው ለዘገባው ስሟ የተቀየረው ህይወት ለዚሁ ማሳያ ናት፡፡

በለጋ ወጣትነት ላይ የምትገኘው ህይዎት እንደምትለው ÷ ምንም ስልጠና ሳትወስድና ምን እና ምን እንደምትሰራ ሳታውቅ ሰነዶች ከተለያዩ ተቋማት በህገወጥ መንገድ ተዘጋጅተው እንደተሰጧት ተናግራለች፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ልክ እንደህይወት በርካቶች ሰለባ መሆናቸውን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

ለሦስት ቀናት በተደረገ ኦፕሬሽንም ከ700 ዜጎች በህገወጦች ተታለው ከሀገር ሊወጡ ሲሉ መያዛቸውን የኤሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ይፋ አድርጓል።

ይህ ህገወጥነት የሚሰራው በህጋዊነት ሽፋን መሆኑን ነው የአገልግሎቱ የኬላዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ቦጋለ የገለጹት፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ምርመራም ደላሎች፣ ኤጀንሲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ምዘና ተቋማት፣ እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች የህገወጥነቱ ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያመላክት መረጃ አግኝቷል።

ከፍተኛ ገንዘብ የከፈሉ ወይንም ‘‘ወደ ስራ ከተሰማራችሁ በኋላ ትከፍላላችሁ’’ የተባሉ በተለይም ከገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ሴቶች በተለይም በህገወጦቹ መረብ ሰለባዎች መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ስልጠና ሳይወስዱ የሙያ ብቃት ማረጋገጫዎች ከመንግስት ተቋማት በገንዘብ ይወጡ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡

ይህ በህገወጥ መልኩ የሚደረግ የሰዎች ዝውውር ለዜጎች ስቃይና መከራ፣ ለሀገርም ገጽታ ብልሽትም ምክንያት ይሆናል፡፡

ለመሆኑ ለዚህ ችግር ተጠያቂው ማን ነው? ኢትዮጵያ አዲስ ህግ ብታወጣም ህገወጥነት የተጫነውን የውጭ የስራ ስምሪት መንገድ ስለምን ማስቆም ተሳናት? ተዋናዮቹ እነማን ናቸው?

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በምርመራ የደረሰበትን መረጃ በተከታታይ ዘገባዎች ወደናንተ ያደርሳል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.