Fana: At a Speed of Life!

ማህበሩ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለኮቪድ 19 መከላከል ግብረ ሃይል ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ለኮቪድ 19 መከላከል ግብረ ሃይል ምግብ ነክ ያልሆኑ ግብዓቶችን አስረከበ።

በርክክቡ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ማህበሩ ከዚም ቀደም ድጋፍ በማድረግ ያሳየውን አጋርነት ዛሬም በድጋሚ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ዶክተር አብርሃም ሌሎችም ተቋማት ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በመሆን ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ እንደተናገሩት፥ ማህበሩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።

ፕሬዚዳንቱ በቫይረሱ ላይ ያለው ግንዛቤ እያደገ ቢመጣም አሁንም የሚታየውን መዘናጋት ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ማህበሩ በዛሬው እለት 2 ሺህ 500 ፍራሽ፣ 2 ሺህ 500 ብርድ ልብስ፣ 2 ሺህ 500 አንሶላ፣ 2 ሺህ 500 ተንቀሳቃሽ የመኝታ ከረጢቶች እንዲሁም ከ20 ሺህ በላይ ሳሙና፣ ማጽጃ ኬሚካሎች እና ሌሎች ድጋፎችን አበርክቷል።

ከእነዚህ መካከል 500 ብርድ ልብሶች፣ 500 አንሶላዎች 500 ፍራሾች፣4 ሺህ ሺህ ሳሙናዎች፣ 600 ማጽጃ ኬሚካሎች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ መከላከል ተግባር የተበረከቱ ናቸው።

ለክልሎች የሚበረከቱት ቁሳቁሶች ከነገ ጀምሮ እንደሚጓጓዙም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዛሬ ያበረከታቸው ቁሳቁሶች ከ7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ናቸው።

በምስክር ስናፍቅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.