Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ እና ኮሚሽኑ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ጉምሩክ ኮሚሽን እየጨመረ የመጣውን የመንገደኞችና የዕቃ ፍሰት ከግምት ውስጥ ያስገባ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እና የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ናቸው፡፡

አቶ መስፍን ጣሰው ከአየር መንገዱ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል ጉምሩክ ኮሚሽን ዋናው መሆኑን ጠቁመው÷ ስምምነቱ የተቀላጠፈ የደንበኞች አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የሁለትዮሽ ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው÷ስምምነቱ እየጨመረ የመጣውን የመንገደኞችና የዕቃ ፍሰት ከግምት ውስጥ ያስገባ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

 

ወደ ሀገር እንዳይገቡ ወይም ከሀገር እንዳይወጡ የተከለከሉና ገደብ የተጣለባቸውን ዕቃዎች በአግባቡ ለመቆጣጠር እና የትራንዚት ዕቃዎች በተቀመጠላቸው አሰራር እንዲስተናገዱ ስምምነቱ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.