ምክር ቤት ምርጫን በተመለከተ የተቀመጡ ሶስት አንቀጾች ላይ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርጫን በተመለከተ የተቀመጡ ሶስት አንቀጾች ላይ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀ።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ልዩ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመሰብሰቢያ አደራሽ ባካሄደው ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል ማስታወቁን በተመለከተ የቀረቡ የመፍትሄ አማራጮችን የውሳኔ ሃሳብ እንዲሁም የብድር ስምምነቶችን ተመልክቷል።
የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጌዴቦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን አለመቻሉን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በምክር ቤቱ መጽደቅን ተከትሎ ቀጣይ ህገመንግስታዊ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርብ በተመራለት መሰረት ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በዚህም ቋሚ ኮሚቴው ምርጫን በተመለከተ የተቀመጡ ሶስት አንቀጾች ላይ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረቡን አስታውቀዋል።
የውሳኔ ሀሳቡ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 54/1 አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 93 ከህገ መንግስት አላማ እና ግቦች እንዲሁም መሰረታዊ መርሆች ጋር ለማስተሳሰር ትርጉም እንዲሰጥባቸው የሚል ህገ መንግስታዊ የመፍትሄ ሀሳብ ነው ያቀረበው።
በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችንና አስታያየቶችን የሰጡ ሲሆን፥ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምን እንዲሳተፉ አልተደረገም? በህገ መንግስቱ ስለምርጫ በግልጽ የተቀምጠ ውሳኔ ለምን ህገ መንግስታዊ ትርጉም አስፈለገው የሚሉ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የምክር ቤቱ አባላት በህግ ባለሙያዎች ምክር ቤቱን መበተን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ፣ ህገ መንግስት ማሻሻልና ህገ መንግስታዊ ትርጓሜን መጠቀም እንደሚቻል ማስቀመጣቸውን ጠቁመው፤ ቋሚ ኮሚቴው ህገ መንግስታዊ ትረጓሜን መሰረት በማድረግ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ተገቢነት ያለው መሁኑንም ያነሱም አሉ።
ከዚህ ቀደም ሕዝቡ ያላመነባቸው አወጆችና ህገ መንግሰታዊ ማሻሻዎች ይደረጉ እንደነበር ያስታወሱት የምክር ቤቱ አባል አቶ ተስፋዬ ዳባ፥ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መቃረን ተገቢነት የለውም ብለዋል።
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ምርጫን ማካሄድ የፌዴራል መንግስትና የምርጫ ቦርድ ሥልጣንና ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ ቦርዱ ምርጫን ለማራዘም ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተጋቢና ህገ መንግስታዊ ነው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ኢ-ህገ መንግስታዊ ናቸው ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ጫላ ለሚ በበኩላቸው፥ ምክር ቤቱ የሚወያይትበት አጀንዳ ሀገርንና ሕዝብን የሚጠቅም፤ እንዲሁም ህገ መንግስታዊ መሆኑን አመልክተው፤ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መቀበል ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጌዴቦ፥ ኮሚቴው የተሰጠውን ሃለፊነት ተቀብሎ ከህገ መንግስቱ ጋር የማይጣረስና አማራጭ የመፍትሄ ሃሳብ ያቀረበ መሆኑን ገልጸው፥ ምክር ቤቱም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ተቀብሎ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል።
ምክር ቤቱም የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማከናወን አለመቻሉን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ በምክር ቤቱ መጽደቅን ተከትሎ ቀጣይ ህገ መንግስታዊ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርብ በተመራለት መሰረት ያቀረበውን የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርጫን በተመለከተ የተቀመጡ ሶስት አንቀጾች ላይ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በ25 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል።
በመቀጠልም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በጣሊያን ሪፐብሊከ መንግስት መካከል ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ክህሎት ማሻሻያ እና ስራ ፈጠራ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እንዲሁም የጤናውን ዘርፍ ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ለሚከናወን በውጤት ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረጉ ሁለት የብርድ ስምምነቶችን አፅድቋል።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከጃፓን አለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ መካከል ለጅማ- ጭዳ እና ሶዶ-ሳውላ የመንገድ ፕሮጄክት ማስፈጸሚያ ያደረገውን የብድር ስምምነት፣ ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር ለአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን አውቶቡስ መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ እንዲሁም ለመሬት መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ፕሮጄክት ማስፈጸሚያ የተደረጉ የብድር ስምምነቶችን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።