Fana: At a Speed of Life!

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የጸና ይሆናል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የጸና እንደሚሆን የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ።

 

የፍትሕ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ዓ.ም ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማስክበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ የክልሉን የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እያወከ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 

በዚህም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቋቋም የማይቻል የጸጥታ መደፍረስ እንዳጋጠመው መግለጹን አስታውሰዋል።

 

የጸጥታ መደፍረስ ተግባሩም በክልሉ ነዋሪ ጫና የፈጠረ መሆኑን በመግለጽ በህገ-መንግስቱ መነሻነት ለፌደራል መንግስቱ  አስፈላጊውን የህግ ማስከበር ስራ እንዲያከናውን ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረዋል።

 

በዚሁ መነሻነትም በፌደራል የጸጥታ ተቋማት እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተገምግሞ አሳማኝ መሆኑን ከግምት በማስገባት የህዝብ ሰላምና ጸጥታ በመጠበቅ ህግና ስርዓትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱን አዋጁ መደንገጉንም ነው የተናገሩት።

 

አዋጁም የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ዓ.ም ተብሎ የሚጠራ መሆኑን አስረድተዋል።

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት በዋናነት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ውስጥ መሆኑ በግልጽ መመላከቱንም አስረድተዋል።

 

ነገር ግን አዋጁ በክልሉ ወይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለን የጸጥታ ችግር የሚያባብስ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለማስቆም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈፃሚነት እንደሚኖረውም አመላክተዋል።

 

ለአዋጁ ተፈፃሚነትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ እንደተቋቋመም ነው ያነሱት።

 

ጠቅላይ መምሪያውም በኢፌዴሪ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል የሚመራ ሆኖ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

 

የዕዙን አባላት፣ መዋቅርና አደረጃጀት በሚመለከትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወሰን መሆኑንም በአዋጁ እንደተገለጸ አንስተዋል።

 

ጠቅላይ መምሪያ ዕዝም የሰዓት እላፊን የማወጅ፣ ለተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋም መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ የማዘዝ ስልጣን ተሰጥቶታል ብለዋል።

 

በሀገረ መንግስቱና በህገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመጣስና አፈፃጸሙን የማደናቀፍ ወንጀል መፈጸሙ፣ መሞከሩ ወይም ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንደሆኑ የጠረጠራቸውን ሰዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር የማዋል  ስልጣን እንደተሰጠውም ነው የገለጹት።

 

ወንጀል ሊፈጸምባቸው የሚችሉ የሚጠረጠሩ እቃዎችንና መሳሪያዎችን ለመያዝ ሌሎች ማስረጃዎችን ለማግኘት ማስረጃዎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በየትኛውም ጊዜ ማንኛውንም ስፍራ የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎችንና ሌሎች ተቋማትን እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችን ለመበርበር ስልጣን ተሰጥቶታልም ነው ያሉት።

 

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተሰጠው ስልጣን መሰረት ደንብና መመሪያ የማውጣት ተፈፃሚ የማድረግ ስልጣን እንደተሰጠው ተናግረዋል።

 

በአማራ ብሔራዊ ክልል ተፈፃሚ እንዲሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ዓ.ም ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የጸና ይሆናል ብለዋል።

 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁ አስፈላጊነቱን አብቅቷል ብሎ በሚያምንበት ጊዜ የአዋጁን ተፈፃሚነት ከስድስት ወራት በፊት እንዲቋረጥ ሊያደርገው እንደሚችልም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.