Fana: At a Speed of Life!

ሊቨርፑል ሞይሰስ ካይሴዶን በከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ ለማስፈረም ስምምነት ላይ ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሊቨርፑል ኤኳዶራዊውን የመሃል ክፍል ተጫዋች ሞይሰስ ካይሴዶን ከብራይተን በእንግሊዝ የዝውውር ታሪክ ክብረወሰን በሆነ ዋጋ ለማስፈረም ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ሊቨርፑል ለካይሴዶ ዝውውር ለብራይተን 110 ሚሊየን ፓውንድ የሚከፍል ሲሆን ተጫዋቹ በዛሬው ዕለት በሊቨርፑል የህክምና ምርመራውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ሊቨርፑል ቀደም ብሎ አርጀንቲናዊውን አማካይ አሌክሲስ ማካሊስተርን ከብራይተን ማስፈረሙ ይታወሳል።

ቀደም ሲል ቼልሲ ለካይሴዶ ዝውውር 100 ሚሊየን ፓውንድ እንዲሁም ባየርንሙኒክ 90 ሚሊየን ፓውንድ ለመክፈል መዘጋጀታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በሌላ በኩል ባየርንሙኒክ ሃር ኬንን ከቶተንሃም ለማስፈረም በመርሃ ደረጃ ከስምምት ላይ ደርሷል፡፡

ዝውውሩ የሚጠናቀቅ ከሆነ የባቫሪያኑ ክለብ ለ30 ዓመቱ አጥቂ 86 ሚሊየን ፓውንድ ፈሰስ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ኬን ለቶተንሃም ሆትስፐርስ 435 ጊዜ ተሰልፎ 280 ጎሎችን በስሙ በማስቆጠር የክለቡ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችሏል፡፡

የቱርኩ ፌነርባቼ ደግሞ ብራዚላዊውን አማካይ ፍሬድን ለማስፈረም ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር በመርሕ ደረጃ መስማማቱ ታውቋል።

እንደ ስካይ ስፖርት ዘገባ ከሆነ ራሱን ለማጠናከር የዝውውር ገንዘብ ያስፈልገኛል ያለው የላንክሻየሩ ክለብ በርካታ ታጫዋቾቹን ለገበያ አቅርቧል።

ክለቡ በሃሪ ማጓየር ዝውውር ከለንደኑ ክለብ ዌስትሃም ጋር ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን፥ በክለቡ ከልጅነቱ ጀምሮ የቆየውን ስኮትላንዳዊ አማካይ ስኮት ማክቶሚናይን የሚገዛ ክለብ ካለም ጥያቄውን ለማድመጥ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የክለቡ አሰልጣኝ ቴን ሃግ ሜሰን ማውንት፣ አንድሬ ኦናና እና ራስመስ ሆይሉንድን ያስፈረሙ ሲሆን፥ የፊዮረንቲናውን አማካይ ሶፊያን አምራባት ፈላጊ መሆናቸውንም ስካይ ስፖርት አስነብቧል።

ከዚህ ባለፈም ከባየርን ሙኒኩ ቤንጃሚን ፓቫርድ እና ከኒሱ ጃን ክሌር ቶዲቦ አንዳቸውን በተከላካይ ቦታ የማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.