በሞሮኮና ሊቢያ በአደጋ ህይወታቸው ያለፉትን ለመዘከር ተጫዋቾች ጥቁር ባጅ ያደርጋሉ – ፕሪሚየር ሊጉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞሮኮ የመሬት መንቀጥቀጥና በሊቢያ የጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመዘከር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሁሉም ተጨዋቾች ጥቁር ባጅ በክንዳቸው ላይ እንዲያደርጉ መወሰኑን ሊጉ አስታውቋል፡፡
የእንግሊዝ ፕረሚየር ሊግ በማህበራዊ ትስስር ገፁ÷ በቅርቡ በሞሮኮ እና በሊቢያ በተከሰቱት አሳዛኝ የተፈጥሮ አደጋዎች ፕሪሚየር ሊጉ በእጅጉ አዝኗል ብሏል፡፡
ከጨዋታው በፊት አሳዛኙ ክስተት ይታወሳል ያለው ፕሪሚየርሊጉ÷ ከጥቁር ባጁ በተጨማሪ ክለቦች እና ተጋጣሚዎቻቸው በሞሮኮ እና ሊቢያ በደረሰው አደጋ የአንድ አፍታ የህሊና ፀሎት እንደሚያደርጉ ገልጿል፡፡
ከነገ ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ በሚደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ከተጨዋቾች በተጨማሪም የክለብ አመራሮች እና የጨዋታ ዳኞች ጥቁር ባጅ አድርገው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሏል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ከኢንተርናሽናል ጨዋታዎች መልስ ነገ 8 ሰዓት ዎልቭስ ከሊቨርፑል በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል።