በሪጋ በሚካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውን አትሌቶች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ርቀቶች በላቲቪያ ሪጋ ነገ በሚካሄደው የዓለም የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ፡፡
5፡50 ላይ በሚካሄደው የ5 ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድር አትሌት እጅጋየሁ ታዬ እና መዲና ኢሳ ሲሳተፉ÷ በዚሁ ርቀት 12፡15 ላይ በሚካሄደው የወንዶች ውድድር አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሀጐስ ገ/ሕይወት ይካፈላሉ፡፡
7፡00 ላይ በ1 ማይል ርቀት በሚከናወነው የሴቶች ውድድር አትሌት ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ኃይሉ የሚሳተፉ ሲሆን÷ በተመሳሳይ ርቀት 7:10 ላይ በሚካሄደው የወንዶች ውድድር አትሌት ታደሰ ለሚ ይሳተፋል፡፡
7፡30 ላይ በሚደረገው የሴቶች የግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌት ጽጌ ገ/ሰላማ፣ ያለምጌጥ ያረጋል እና
ፍታው ዘርዬ የሚካፈሉ ሲሆን÷ በዚሁ ርቀት 8:15 ላይ በሚካሄደው የወንዶች ውድድር አትሌት ጀማል ይመር፣ ንብረት መላክ እና ፀጋዬ ኪዳኑ እንደሚሳተፉ ተመላክቷል፡፡
ሁሉም ውድድሮች በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ቀን ላይ እንደሚካሄዱ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡