Fana: At a Speed of Life!

ፔር ሉዊጂ ኮሊና – የዓለማችን ምርጡ የእግር ኳስ ዳኛ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፈረንጆቹ 1998 እስከ 2003 ለሥድስት ተከታታይ ዓመታት “የዓለማችን ምርጡ ዳኛ” የሚል ማዕረግ ሰጥቶታል፡፡

በፈረንጆቹ የካቲት 13 ቀን 1960 በጣሊያን ቦሎኛ የተወለደው ፔር ሉዊጂ ኮሊና የዳኝነት ሕይወቱን በ18 ዓመቱ የጣሊያን ሴሪ ሲ 1 ጨዋታ በመዳኘት “ሀ” ብሎ ጀመረ፡፡

በእግር ኳስ ዳኝነት ብቃቱ የተመሰከረለትን ኮሊና የ“ቫር” ሥርዓት ባልተጀመረበት ጊዜ እንኳ የሜዳ ላይ ስህተቶች እንደማያመልጡት ምስክርነት የተሰጠው ነው።

ዳኛው በሜዳ ውስጥ ካሉ ተጫዋቾች ጋር በ4 ቋንቋዎች ማለትም በፈረንሳይኛ፣ ስፓኒሽ፣ ጣሊያንኛ እና እንግሊዝኛ መግባባት ይችል ነበር።

ከእያንዳንዱ ጨዋታ በፊት ጨዋታውን እና የሚያጫውታቸውን ቡድኖች ተጫዋቾች በማጥናት የተጫዋቾችን ሥም ይይዝ ነበር።

በፈረንጆቹ 2002 ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ በጥምረት ባዘጋጁት የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ብራዚላዊው ኮከብ ሮናልዶ ማሊያውን አውልቆ ከኳስ ጋር በአክብሮት የሠጠው ዳኛ ነው – ፔር ሉዊጂ ኮልሊና።

በጨዋታው ባሳየው ብቃትም የብራዚል እና የጀርመን ተጫዋቾች ክብራቸውን በግልፅ ለግሰውታል፡፡

እግር ኳስ ተጫዋቾች በእሱ የሚዳኙ ከሆነ ክብር እና ፍርሃት በአንድ ላይ ይሰማቸው ነበር፡፡

በቪዲዮ ጌሞች ውስጥ የሚታይ ብቸኛው ዳኛም ነው፡፡

በፈረንጆቹ 2005 ላይ ሜዳ ገብቶ መዳኘት ቢያቆምም እስከ አሁን ድረስ ከእግር ኳሱ ዓለም ራሱን ሳያገል በጣሊያን የእግር ኳስ ማኅበር ውስጥ የማማከር ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡

እስከ ፈረንጆቹ 2010 የዩክሬን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ኃላፊም በመሆን አገልግሏል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የእግር ኳስ ማኅበር የዳኞች ኮሚቴ አባል እና የፊፋ የዳኞች ኮሚቴም ነበር፡፡

ራሰ-በራ፣ ባለ ብሩኅ ሰማያዊ ዓይን፣ የ 1 ሜትር ከ88 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ቁመት ባለቤት የኢኮኖሚክስ፣ ምሩቅ ዳኛ ፔር ሉዊጂ ኮልሊና በቅፅል ሥሙ “ዘ ሼሪፍ” በመባልም ይታወቃል፡፡

በዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.