Fana: At a Speed of Life!

ኔማር  ባጋጠመው ጉዳት ከ8 እስከ 10 ወራት ከጨዋታ ሊርቅ ይችላል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብራዚላዊው ኮከብ ኔማር ጁኒየር ባጋጠመው የመገጣጠሚያ ጉዳት ከ8 እስከ 10 ወራት ከጨዋታ ሊርቅ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የተጨዋቹ ጉዳት 90 ሚሊየን ዩሮ ፈሰስ በማድረግ ተጨዋቹን ከፒ ኤስ ጂ ላስፈረመው የሳውዲው ክለብ አል ሂላል መጥፎ ዜና ነው ተብሏል፡፡

የ31 ዓመቱ አጥቂ በአለም ዋንጫ ማጣሪያው ብራዚል ከኡራጓይ ባደረጉት ጨዋታ የኡራጓዩ የመሀል ክፍል ተጨዋች ኒኮላስ ዲ ላ ክሩዝ ባደረሰበት ጫና ሚዛኑን ባለመጠበቁ ከፍተኛ የመገጣጠሚያ ጉዳት አጋጥሞታል፡፡

በኡራጓይ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የሞንቶቪዶው ጨዋታ ኔማር ከእረፍት በፊት ባጋጠመው ጉዳት በሀዘን ስሜት ከሜዳ መውጣቱም የሚታወስ ነው፡፡

ቢቢሲ ስፖርት በዛሬው እለት እንዳስነበበውም የአል ሂላል እና የብራዚሉ የፊት መስመር አጥቂ ኔማር ጁኒየር ቀዶ ጥገና ይደረግለታል የተባለ ሲሆን÷ በጉዳቱ ከ8 እስከ 10 ወራት ከሜዳ ሊርቅ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

የብራዚል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኤድናልዶ ሮደርጊየዝ÷”መላው አለም እና ብራዚላውያን የኔማርን ጤንነት አብዝተው ይመኛሉ ፣እሱ ሜዳ ላይ ሲኖር እግርኳስ ደስ ይላታል” ብለዋል፡፡

በጉዳት እየተቸገረ የሚገኘው ኔማር ጁኒየር ቀደም ሲል በተካሄደው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ባጋጠመው ጉዳት ሀገሩ ብራዚል ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች ሳይሰልፍ መቅረቱ አይዘነጋም፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.