Fana: At a Speed of Life!

አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት ‘የኛ ምርት’ የተሰኘ አውደርይና ባዛር ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ አውደርዕይና ባዛር ”ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ተከፍቷል፡፡
አውደርዕይና ባዛሩ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና የፌዴራልና የክልል ተቋማት አመራሮች በተገኙበት ነው የተከፈተው፡፡

አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ ኃብት ሊቀየሩ የሚችሉ የበርካታ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት ሀገር ናት ሲሉ አውስተዋል።

የተፈጥሮ ፀጋን ወደ ኃብት ለመቀየር የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ገበያና ፈጠራ እንዲሁም ሀገራዊ ፍላጎትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን አመዛዝኖ መሥራት ይጠይቃልም ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻር መንግሥት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች በሰጠው ትኩረት በርካታ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት መቻሉን አመላክተዋል።

የአምራች ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም አፈ-ጉባዔው አረጋግጠዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው÷ መንግሥት በ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ከለያቸው አምስት የኢኮኖሚ የትኩረት መስኮች የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ ነው ብለዋል።

በዚህም የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ የብድር አቅርቦት፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታና የገበያ ትስስር በመፍጠር ዘርፉን እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል።

ከ100 በላይ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ግብርና ማቀነባበር፣ በኢንጂነሪንግ ምርቶችና በፈጠራ ስራዎች የተሰማሩ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተሳትፈዋል፡፡
ሀገር አቀፍ አውደርዕይና ባዛሩ ከታሕሳስ 3 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለሸማችና ጎብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.