Fana: At a Speed of Life!

ጋናዊቷ ከ5 ቀናት በላይ ሳታቋርጥ በማዜም የዓለም ክብረ-ወሠን ሰበረች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፉዋ አሳንቴዋ ኡዉሱ አዱዎነም የተባለች ጋናዊት ዘፋኝ የዓለም ክብረ-ወሠን ለመስበር ከአምስት ቀናት በላይ ያለማቋረጥ ማዜሟ ተነግሯል፡፡

አፉዋ አሳንቴዋ ÷ “ሲንግ ኤ ቶን” በሚል ርዕስ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ዋና ከተማ አክራ ያለማቋረጥ መዝፈን የጀመረችው በፈረንጆቹ የገና በዓል ዋዜማ መሆኑን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ሀገርኛ ዜማዋን ለ126 ሠዓታት እና 52 ደቂቃዎች ለታዳሚዎቿ ካቀረበች በኋላ ባሳለፍነው ዐርብ ማጠናቀቋም ነው የተመላከተው፡፡

በመርሐ-ግብሩ የቀድሞውን የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ፣ የአሁኑን ምክትል ፕሬዚዳንት ማሃማዱ ባዉሚያ ጨምሮ በርካታ ጋናዊያን ተገኝተው የሚያስደንቅ ድጋፍ ሲያደርጉላት እንደነበርም ተገልጿል፡፡

ጋናዊቷ ዘፋኝ ÷ ለ105 ሠዓታት ባለማቋረጥ በመዝፈኑ የዓለም ክብረ-ወሠን ይዞ የቆየውን ሱኒል ዋግሜር የተባለ ሕንዳዊ ሙዚቀኛ ከመንበሩ እንዳወረደችውም ነው የተነገረው፡፡

ሕንዳዊው ሙዚቀኛ ሱኒል ÷ በጋናዊቷ አፉዋ አሳንቴዋ በ21 ሠዓታት እስኪበለጥ ድረስ ክብረ ወሰኑን ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ ይዞ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡

ጊነስ ወርልድ ሬከርድስ በፌስ ቡክ ገጹ የደረሰውን መረጃ ተከትሎ ምላሽ መስጠቱም ነው የተገለጸው፡፡

የዓለም ድንቃ ድንቅ ሁነቶችን የሚመዘግበው ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ ÷ ዳኞቹ ትክክለኛ መረጃ እንዳገኙ ጋናዊቷ ዘፋኝ አፉዋ አሳንቴዋ በትክክል የግለሰቡን ክብረ-ወሰን ሰብራለች ወይም አልሰበረችም የሚለውን የሚወስን ይሆናልም ብሏል፡፡

ሁነቱ ከወሩ ቀደም ብሎ ጋና በፈረንጆቹ ገና ቱሪስቶችን ለመሳብ እና ባሕሏን ለማስተዋወቅ ከጀመረችው “ቢዮንድ ዘ ሪተርን” የሚል ለጎብኚዎቿ ቪዛ የማመቻቸት ዘመቻ ጋር መግጠሙንም ነው መረጃው ያመላከተው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.