Fana: At a Speed of Life!

ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ምርታማነት ማደግ የሚጫወቱትን ሚና ማጠናከር አለባቸው ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 26 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ምርታማነት ማደግ የሚጫወቱትን ሚና ማጠናከር እንደሚገባቸው የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አመለከቱ።

 

ሀገር አቀፍ የኀብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጓል።

 

ሪፎርሙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብርና፣ በቁጠባና ብድር፣ በኢንቨስትመንት መስክ የሚጫወቱትን ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው ተብሏል።

 

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፥ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ ግብዓቶች በማቅረብ አምራቹ ባመረተው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ በኩል አበረታች ጅምሮች አሉ።

 

እንዲያም ሆኖ ቴክኖሎጂዎችን በጥራትና በብዛት ማቅረብና ገበያን ማረጋጋት አሁንም የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

 

ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲያመጡ በመስኩ የለውጥ ሥራዎችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፥ ሚኒቴሩም በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ማህበራትን ለማጠናከር እንዲሁም የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው በገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል 50 ቢሊየን ብር በቁጠባና በዕጣ ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

 

በዚህም ለአርሶና አርብቶ አደሩ በአማካይ በዓመት 12 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ብድር እየቀረበ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችና እንዲሁም የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብሮች ላይ በመሳተፍ ወገናዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን አብራርተዋል።

 

በአሁኑ ወቅት በገጠርና በከተማ ከ28 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ አባላት ያሏቸው ከ110 ሺህ በላይ መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንደሚገኙ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።

 

403 ዩኒየኖች እንዲሁም 5 ፌዴሬሽኖች ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በግብርና፣ በሸማቾች፣ በቁጠባና ብድር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ተደራጅተው ከ49 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት መቻላቸውም ተጠቅሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.