Fana: At a Speed of Life!

የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገር አቀፍ የችቦ ቅብብሎሽ በመቀሌ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገር አቀፍ የችቦ ቅብብሎሽ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በመቀሌ ከተማ ተከሂዷል።

በችቦ ቅብብሎሽ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።

መርሐ-ግብሩ በመጪው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው 33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ በማህበረሰቡ ዘንድ ከወዲሁ መነቃቃትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አትሌት ደራርቱ በወቅቱ እንደተናገሩት÷ የኦሎምፒክ ችቦው ወደ ሁሉም ክልሎች ጉዞ ካደረገ በኋላ ሐምሌ 6 ቀን 2016ዓ.ም በአዲስ አበባ ፍፃሜውን ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች ከትግራይ ክልል ወጥተዋል ያሉት ረዳት ኮሚሽነሯ÷ በቀጣይም ተተኪዎችን ለማፍራት ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል።

ኦሎምፒክ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ የኦሎምፒክ ችቦው በመላው ሀገሪቱ ሲዘዋወር የኢትዮጵያን አንድነት የምናጠናክርበት መሆን አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

ቀጣይ ተረኛ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ችቦውን እንደተረከበ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የክልል አመራር አባላት በመገኘት የኦሎምፒክ ችቦውን በመያዝ የእግር ጉዞ የተደረገ ሲሆን÷ የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖችም ተስተናግደዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.