ሃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በወላይታ ሶዶ ያስገነባው ባለ 4 ኮከብ ሆቴል ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በወላይታ ሶዶ ከተማ ያስገነባው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል በዛሬው ዕለት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ÷ ሆቴሉ 107 ምቹና ዘመናዊ መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ ከ15 እስከ 500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ሰባት ሁለገብ አዳራሾች እንዳሉት ተናግሯል፡፡
ከዚህ ባለፈም የጤና መጠበቂያ ሥፍራዎች፣ ሶስት ሬስቶራንቶች እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎችን እንደያዘ አስረድቷል፡፡
ሆቴሉ አሁን ላይ 160 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን÷ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ለ300 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡
ሃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በቅርቡ በኮንሶ፣ ደብረ ብርሃን እና ጅማ ከተሞች ተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን ለመክፈት እየሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
በታሪኩ ወ/ሰንበት