Fana: At a Speed of Life!

የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ሊያረጋግጥ የሚችል አርበኛ ትውልድ መገንባት ይገባል – አቶ መለሰ ዓለሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐሰት ትርክቶችን በማረም የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ሊያረጋግጥ የሚችል አርበኛ ትውልድ መገንባት እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ

“ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን እና ከደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በደብረ ማርቆስ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በማስቆም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ለጋራ ሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ ለማስቀመጥና ሕዝባዊ አንድነት ለመፍጠር ያለመ ውይይት መካሄዱም ነው የተጠቆመው።

በአቶ መለሰ ዓለሙ የመነሻ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ በየአካባቢው የተከሰተውን የሰላም እጦት ችግሮችን በመለየትና በማረም ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ማረም ይገባልም ብለዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ቴንኩዌይ ጆክ፥ ሁላችንም እኩል ተጠቃሚ የምንሆንባት ኢትዮጵያን መገንባት ይገባል ብለዋል።

ከምንም በላይ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልምና ሁሉም አካል በጋራ ለሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ መንግሥት በሁሉም አካባቢ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

መንግሥት ከሚያከናውነው ሥራ ባለፈ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመው፥ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ ዓለሙ፥ ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ምንጩን መለየትና የመፍትሔ አማራጮችን ማስቀመጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይመለሱ ዘንድ ቅድሚያ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም የሚነሱ የሐሰት ትርክቶችን በማረም የአንድነት ትስስራችንን ማጠናከርና የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ሊያረጋግጥ የሚችል አርበኛ ትውልድ መገንባት ይገባልም ብለዋል፡፡

መንግሥት በሕዝቡ የሚነሱ ሁለንተናዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራም ነው አቶ መለሰ ያረጋገጡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.