Fana: At a Speed of Life!

ለሽብር ወንጀል ሊውል የነበረ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሽብር ወንጀል ሊውል የነበረ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ መያዙን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪው ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በመመሳጠር እና በመገናኘት የጥፋት ተልዕኮ ለመፈፀም መነሻውን ከአማራ ክልል ወልድያ ከተማ በማድረግ በግለሰብ እጅ የማይያዙ ሕገ-ወጥ የቡድን የጦር መሣሪያዎች ለሽብር ቡድኑ ሊያደርሰ ሲል ነው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡

በዚኅም አንድ አር ቢ ጂ ላውንቸር እና አንድ ብሬን፣ አምስት አጭር ርቀት መገናኛ ሬድዮ እና አራት ቻርጆችን በፒክ-አፕ መኪና ጭኖ ወደ ኦሮሚያ ክልል ኤጀሬ አካባቢ ለሽብር ቡድኑ ሊያደርስ ሲንቀሳቀስ ልዩ ቦታው አሸዋ ሜዳ በተባለ አካባቢ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር የጦር መሣሪያው ከነ-ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን እያጣራበት እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

እነዚህ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በሽብር ቡድኑ እጅ ቢገቡ ኖሮ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ይችሉ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመቆጣጠር በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን ለመቆጣጠር የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.