Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና ማሳለጥ እና ሰላምና ፀጥታን ማስጠበቅ የአህጉሪቷ ቀጣይ ትኩረት ሊሆን ይገባል – የቀድሞ የሕብረቱ ሊቀመንበር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካን አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ማሳለጥ እና ሰላምና ፀጥታን ማስጠበቅ የአህጉሪቷ ቀጣይ ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ የቀድሞ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ሞሪታኒያ የ2024 አፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ከኮሞሮስ ተረክባለች።

የቀድሞው የሕብረቱ ሊቀመንበር የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ ÷ በሕብረቱ የሊቀመንበርነት ዘመናቸው ያከናወኗቸውን ተግባራት በዝርዝር አስረድተዋል።

በተለይም በሰላምና ፀጥታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ መሠረተ-ልማትና ሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

የተጠናቀቀው 2023 የአፍሪካን የጋራ ጥቅም በዓለም መድረኮች በማስጠበቅ ውጤት የተገኘበት ዓመት እንደነበርም አንስተዋል።

ለአብነትም በቡድን ሰባት (ጂ-7) ጉባዔ፣ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ ጉባዔ፣ በአፍሪካ ጣሊያን መድረክ እንዲሁም በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደው የአውሮፓ ሕብረት ስብሰባዎችና በሌሎችም መድረኮች ላይ የአፍሪካን ድምፅ ማሰማት ተችሏል ብለዋል።

በዚህም የአፍሪካን ጥቅምና በዓለም መድረክ ያላትን ቦታ ከፍ የሚያደርጉ ውጤቶች መገኘታቸውን ነው የገለጹት፡፡

በኢኮኖሚ መስክም የአፍሪካን እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን ጠቁመው ÷ ይህንን ተግባር የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰላምና ፀጥታ፣ የአፍሪካን ውክልና በዓለም መድረክ ማስጠበቅ ከነበሩ ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ውስጥ ዘርዝረዋል።

ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን፣ በ2063 አንድነቷ የተጠናከረና የበለፀገች አህጉርን እውን ለማድረግ መሠረት በመሆኑ በትኩረት ከተሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአህጉሪቱ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የግልና የመንግሥት አጋርነት ለማጠናከርም የተከናወኑ ተግባራትን በመጠቆም የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በቀጣይም አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ተስፋ የሚጣልበት ጥረት መደረጉን ገልፀዋል።

#Ethiopia #Africa

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting/
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.