Fana: At a Speed of Life!

የሀሪ ኬን የዋንጫ እርግማን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቶተንሃም እና የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪው ሃሪ ኬን ከአዲሱ ትውልድ ምርጥ አጥቂዎች ውስጥ ስሙ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

በእግር ኳስ ሜዳ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ቢያደርግም ዋንጫ አንስቶ በመሳም ረገድ ግን ዕድል ከእሱ ጋር አይደለችም።

የ30 ዓመቱ አጥቂ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ባደረጋቸው ጨዋታዎች የዋንጫ ክብርን ማሳካት አልቻልም፡፡

እንግሊዛዊው አጥቂ ሀሪ ኬን አሁን እየተጫወተበት ያለው የጀርመኑ ባየርን ሙኒክ ትናንት ባደረገው ጨዋታ መሸነፉን ተከትሎ በእግር ኳስ ዘመኑ የመጀመሪያውን ዋንጫ የማንሳት ተስፋው ደብዝዟል።

ተጫዋቹ በእግር ኳስ ህይወቱ ያጋጠውን የዋንጫ እርግማን ለመስበር ባለፈው ዓመት የክረምት የዝውውር መስኮት የባባሪያኑን ክለብ ባየርን ሙኒክ ቢቀላቀልም ክለቡ በቡንደስሊጋ ጨዋታዎች ያጋጠመው ተደጋጋሚ ሽንፈት የሃሪ ኬንን ምኞት አጣብቒኝ ውስጥ ከቶታል፡፡

በተለይም ባየርን ሙኒክ በመሪው ባየርን ሊቨርኩስን ባለፈው ሳምንት 3 ለ 0 በሆነ ውጤት የተሸነፈ ሲሆን ትናንት ምሽት በተደረገ ጨዋታ ደግሞ ሙኒክ በአዲስ አዳጊው ቦቹም 3 ለ 2 ተሸንፏል፡፡

በዚህም ሙኒክ ከመሪው ባየርን ሊቨርኩሰን ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት የሰፋ ሲሆን 14 ጨዋታዎች በቀሩት የቡንደስሊጋው መርሃ ግብር ሃሪ ኬንም ሆነ ባየርን ሙኒክ የዋንጫ ተስፋቸው በእጅጉ ጠቧል፡፡

ሃሪ ኬን በ2018/19 የውድድር ዘመን በሻምፐዮንስ ሊጉ ፍፃሜ ቶተንሃም በሊቨርፑል 2 ለ 1 በመሸነፉ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ሲያጣ በዚሁ የውድድር ዓመት በካራባኦ ካፕ ቶተንሃም ለፍፃሜ ቢደርስም በማንቼስተር ሲቲ ተሸንፎ ዋንጫውን አጥቷል፡፡

በተጨማሪም በዩሮ 2020 ከእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ጋር ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ የቻለው ኬን በፍፃሜው እንግሊዝ በጣሊያን በመለያ ምት በመሸነፏ ዋንጫውን ማንሳት ሳይችል ቀርቷል፡፡

የአራት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ የወርቅ ጫማ አሸናፊው ሀሪ ኬን ከባየርን ሙኒክ ጋር በሻምፒዮንስ ሊጉ እስከ ዋንጫ ይጓዛል ወይስ የባየርን ሊቨርኩስንን ነጥብ መጣል ጠብቆ የሊጉ ሻምፒዮን ሊሆን ይችላል የሚለው በቀጣይ የውድድር ጊዜያት የሚታይ ይሆናል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.