Fana: At a Speed of Life!

የአጥንት ህመም አይነቶችና ምልክቶች

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰው ልጅ ያለ አጥንት፣ መገጣጠሚያ እና ተያያዥ የሰውነት አካላት ቆሞ መራመድም ሆነ መቀመጥ፣ መነሳት በጥቅሉ መንቀሳቀስ አይችልም።

የሰውነትን ክብደት ሙሉ ለሙሉ የሚሸከመው አጥንት ሲሆን÷ በዚህም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ አጥንት ላይ ከፍተኛ ጫና ከመብዛቱ ባለፈ በተለያዩ አደጋዎች ሳቢያ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ አደጋ ይደርስበታል።

ይህንን ተከትሎ የአጥንት ጤና ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ውስጥም ቀጥሎ የተዘረዘሩት ይጠቀሳሉ፡-

– አደጋዎች ምክንያት የሚመጣ የአጥንት ስብራትና የመገጣጠሚያ አካላት ውልቃት – የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዋናነት በትራፊክና በግንባታ ቦታ በሚደርሱ ልዩ ልዩ አደጋዎች ሳቢያ የሚከሰት ነው።

– በተጨማሪም በመውደቅ፣ በዱላና በድንጋይ በመመታት፣ በጦርነትና በግጭት ጊዜ፣ በሥራ ቦታ በማሽን በመቆረጥ፣ አጥንት ሲሳሳ በትንሽ ምክንያት መሰበር … ወዘተ የአጥንት ስብራትና የመገጣጣሚያ አካላት ውልቃት የሚያጋጥሙበት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

– ሌላው በቂ የፀሐይ ብርሃን ካለማግኘት ጋር ተያይዞ በቫይታሚን ዲ እጥረት ሳቢያ የአጥንት መሳሳት፣ መጣመም፣ የተለያዩ ቦታዎች ላይ መሰበር ነው፡፡

– እንዲሁም የእግር መቆልመምና መጣመም፣ የጀርባ መንጋደድ፣ የጉልበት መጣመም፣ የቅርጽ መበላሸትና ሌሎች በተፈጥሮ የሚመጡ የአጥንት ህመሞች በስፋት ይስተዋላሉ።

– የአጥንት ካንሰር እና እጢም የአጥንት የጤና ችግሮች ናቸው፤ የአጥንት ካንሠር ልክ እንደሌሎች የካንሰር አይነቶች በጊዜ ከተደረሰበት ስለሚድን፤ ችግሩ የገጠማቸው ሰዎች ህመሙ ስር ሳይሰድ በጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ህክምና መከታተል ይኖርባቸዋል።

– ሌላው ከባህላዊና ዘመናዊ የስፖርት ጨዋታዎች ጋር ተያይዞ የሚመጡ እና ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጡ የአጥንት የጤና ችግሮች አሉ።

በአጠቃላይ አጥንት ለተለያዩ ጉዳቶች የተጋለጠ በመሆኑ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ለአጥንት ጥንካሬ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለአጥንት ጥንካሬ የሚጠቅሙ ሙዝ፣ ወተት እና የወተት ተዋፅኦዎች እንዲሁም አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠሎችን የመሳሰሉ በካልሺየም የበለፀጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ ይመከራል ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው በብዛት የካርቦን ይዘታቸው ከፍ ያለና ጣፋጭ ለስላሳ መጠጦችን ጨምሮ፣ ለረጅም ጊዜ የሚወሰዱ መድሀኒቶችን (ስቴሮይድ፣ ወዘተ) የሚጠቀሙ፣ በርካታ አልኮል የሚጠጡና ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ለአጥንት መሳሳት፣ መሰበር እና መበስበስ ሊጋለጡ ይችላሉ።

ስለዚህ ማንኛውም ሰው ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ማድረግና አጥንትን የሚያጠነክሩ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ እንዳለበት ይመከራል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.