Fana: At a Speed of Life!

ለአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገት የተጠናከረ አህጉራዊ የንግድ ሰንሰለትን መገንባት ወሳኝ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገት የተጠናከረ አህጉራዊ የንግድ ሰንሰለትን መገንባትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገለጹ፡፡

አህጉራዊ የንግድ ሰንሰለትን ለማስፋፋትና የአፍሪካ ሀገራት የጉምሩክ እንቅስቃሴያቸውንና ተሞክሮዎቻቸውን ለመለዋወጥ ያለመ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የጉምሩክ እና ወደብ አስተዳደር አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በወቅቱ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ግልጽነትን ተላብሶ አሰራርን በማጎልበትና በማዘመን ህገወጥ ንግድን በመከላከልና ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የሀገር እድገትን ለማፋጠን እየሰራ ነው።

ለአፍሪካ ኢኮኖሚ እድገት የተጠናከረ አህጉራዊ የንግድ ሰንሰለትን መገንባትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ጠቁመው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ለመስራት በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ አንስተዋል።

ህገ ወጥ ንግድ አሁንም ለአህጉሪቱ እድገት ማነቆ እየሆነ መምጣቱን የገለጹትኮሚሽነሩ÷ ይህን ህገ ወጥ ተግባር በመከላከሉ ረገድ በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የተጠናከረ የንግድ ሰንሰለት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ተፅዕኖ እንደፈጠረባት ገልጸው÷ ለዚህም ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ መጀመሯን በመግለጽ ለውጤታማነቱ የቅንጅት ስራ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መድረኩን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው የአፍሪካ ሊደርሽፕ ድርጅት ጋር በመተባበር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሳሙኤል ወርቃየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.