Fana: At a Speed of Life!

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ አበረታታለሁ – ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተለያዩ የማበረታቻ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሐሰን ገለጹ፡፡

በዚሁ መሠረት÷ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚከፈለው ታክስ 15 በመቶ እና በከፊል ተገጣጥመው ለሚገቡ ደግሞ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችም ከታክስ ነጻ መደረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡

ይህም በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ከሚጣለው ታክስ አንጻር አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት እየሠራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

የጥገና ማዕከል እና የቻርጅ ስቴሽን እጥረት እንዳይኖር እየተሠራ መሆኑን ገልጸው÷ አሁን ላይ በአዲስ አበባ 60 የቻርጅ ስቴሽኖች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በ10 ዓመትም በአዲስ አበባ 1 ሺህ 176 እንዲሁም በክልል ከተሞች 1 ሺህ 50 የቻርጅ ስቴሽኖችን ለመሥራት ታቅዷል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

439 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በ10 ዓመት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.