Fana: At a Speed of Life!

በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች ሐሳባቸውን አጀንዳ እንዲያደርጉ ማበረታታት እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች ሐሳባቸውን በማውጣት አጀንዳ እንዲያደርጉ ማበረታታት እንደሚገባ አስገነዘቡ፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሀገራዊ የምክክር መድረክ የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላትን የሚያሳትፍ እና ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም በርካታ ሀገራት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሀገራችንም የሐሳብ ልዩነት እየሰፋ ከዚህም አልፎ ግጭቶች እየተከሰቱ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ይህን ለማስተካከል እና ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር ለሚደረገው ጥረት የምክክር ኮሚሽኑ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም በግጭቶች በተለይም ሴቶች ተጎጂ ስለሚሆኑ ይህን ለማስቀረት እንዲቻል ሐሳብ በሚዋጣበት እና ውሳኔ በሚሰጥበት ሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ሐሳባቸውን አውጥተው አጀንዳ እንዲያደርጉ ሴቶችን ማበረታታት አለብን ብለዋል።

በትዕግስት አስማማው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.