Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ እርሻ ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፈነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ እርሻ እስካሁን ድረስ ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ሃላፊው አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ እንዳሉት ፥ በክልሉ ከ741 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ እርሻ ለማልማት ታቅዶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

የእርሻ ዝግጅቱ 95 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ፥ ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳም በዋና ዋና ሰብሎች በዘር ለመሸፈን መቻሉን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የሚያስፈልገው ከ401 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎች እንዲሁም ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ከልማቱም ከ68 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ያመለከቱት አቶ ሃይለማርያም ፥ ይህም ከአምናው የበልግ እርሻ የ15 በመቶ ብልጫ እንዳለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በበልግ ለማግኘት የተያዘውን ምርት ለማሳካት ባለድርሻ አካላትና አመራሩ ሳይለማ የሚቀር መሬት እንዳይኖር ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በተያዘው ዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት በክልሉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ አምራች ለመሆን ግብ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነም ነው ያነሱት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.