አቶ ሽመልስ አብዲሳ መንግሥት ጥንካሬዎችን እየለየና ክፍተቶችን እያረመ ስኬት ማስመዝገቡን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ሥራዎችን በየጊዜው እየገመገመ ጥንካሬዎችን እየለየ እና ክፍተቶችን እያረመ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
የኦሮሚያ ክልል የ2016 በጀት ዓመት 3ኛ ሩብ ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩም የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባዔ ሰዓዳ አብዱራህማን፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፈቃዱ ተሰማን ጨምሮ ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ አመራሮች ተገኝተዋል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር መንግሥት ባለፉት ዓመታት ዕቅዶችን ቀርፆና ግልፅ አሠራሮች ዘርግቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ሥራዎችን በየጊዜው እየገመገመ ያሉ ጥንካሬዎችን እየለየ እና ክፍተቶችን እያረመ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ብለዋል።
ዕቅድ የችግሮቻችን መፍቻ፣ ጥንካሬዎችን ማስቀጠያና ክፍተቶች ማረሚያ፣ የልማት ዕድሎችን መለያና ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየሪያ መንገድ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ሁሉም ዞኖችም እኩል ማቀድና መፈፀም እንደሚገባቸው አስገንዝበው÷ በዕቅድ አፈፃፀም ላይ የሚታዩ ልዩነቶችን ማረቅ እንደሚገ አሳስበዋል።
በቀሪው ሩብ ዓመትም ያልተሳኩ ዕቅዶችን መፈፀም ላይ ትኩረት በማድረግ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድም ይህን ባገናዘበ ሁኔታ መዘጋጀት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
አቶ ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው የግምገማ መድረኩ እየተካሄደ ያለው÷ የክልሉን መንግሥትና የፓርቲ የሥራ አፈፃፀም ስኬቶችን እና ጉድለቶችን በመለየት ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል፣ ፈተናዎችን ለመፍታትና ዳግም ወደ ዕድል ለመቀየር ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩም የክልሉ መንግሥትና በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፓርቲ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን÷ በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይም ምክክር እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡
በመራኦል ከድር