Fana: At a Speed of Life!

ፓርቲው ያጋጠሙትን ፈተናዎችና ጫናዎች በፅናት በማለፍ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድል እያስመዘገበ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል ያጋጠሙትን ፈተናዎችና ጫናዎች በፅናት በማለፍ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድል እያስመዘገበ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

”ቃል በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የፓርቲው ኮንፍረንስ በአዳማ አባገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚ ስብራትን መጠገን የሚያስችል መሰረት የተጣለበት ተግባር አከናውኗል።

ፓርቲው ሀገሪቱ ከነበረችበት ችግሮች እንድትወጣ በሙሉ አቅሙ በመስራት በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ድል እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በፈተናዎችና ጫናዎች ተስፋ ሳንቆርጥ መላው ህዝቡንና አባላቱን በማሰባሰብ ድል አስመዝግበናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ኮንፍረንሱ ያሉትን ችግሮች በመለየት ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ነው ያሉት።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተኩል የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅዶችን በአግባቡ በመለየት በጥራትና በፍጥነት መፈፀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ብልሹ አሰራር፣ ሌብነትና ህገ-ወጥ ተግባራትን በማረምና ስርዓት በማስያዝ የብልጽግና ጉዞን በአንድነት ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው÷ ፓርቲው ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በማንገብ አመርቂ ድል እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲው ሀገራዊ ማንነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት መሰረት ያደረገ የጋራ ትርክት ለመገንባት በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በመጀመሪያው የፓርቲው ጉባኤ ላይ የተቀመጡትን አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል።

በዚህም በምግብ ራስን ለመቻል፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በጥራትና በብዛት በማምራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.