Fana: At a Speed of Life!

50 የእጅ ቦምብ ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 50 የእጅ ቦምብ ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገመንግስታዊና በህገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጠ።

በክስ መዝገቡ ተካቶ የነበረ ደጋጋ ፈቀደ የተባለ 3ኛ ተከሳሽ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው በመከላከሉ ፍርድ ቤቱ በነጻ አሰናብቶታል።

ጥፋተኛ በተባሉት ተከሳሾች አማንኤል ግርማ እና አብዶ መላኩ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 9/ሐ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ነው ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 10/2013 መሰረት ሽብርተኛ ብሎ የተሰየመውን ሸኔ የሽብር ቡድንን በቀጥታ እየረዱ መሆኑን እያወቁ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀሰዉ የሸኔ ሽብር ቡድን ታጣቂዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን፤ ተተኳሽ ጥይት በማቅረብ እና ድጋፍ ማድረግ ላይ ተሰማርተዉ እንደነበር በቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ላይ ተመላክቷል።

በተለይም 1ኛ ተከሳሽ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀስ የሸኔ ሽብር ቡድን አባል ከሆነዉ ነጋሳ ምሬሳ (አዱኛ ተስፋዬ) ከተባለ ሰዉ ጋር በመገናኘት በነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም የሽብር ቡድኑ አባል ነው የተባለው ግለሰብ ካሳሁን በተባለ ሰዉ አማካኝነት ከአፋር ክልል አዋሽ ከተማ ቦምብ ይዞ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ እና ተቀሎ ”እኔ በምልከዉ ሌላ ሰዉ ትልክልኛለህ” በማለት እንደተነገረው ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል።

ይኸው 1ኛ ተከሰሽም በጉዳዩ በመስማማት ጓደኛዉ ለሆነው ለ2ኛ ተከሳሽ ጉዳዩን በማሳወቅና ቦምቡን አብረው ሄደው ተቀብለው ለማምጣት በመስማማት በነጋታው ማለትም በነሐሴ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በአ/አ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታዉ ጋርመንት ወደሚባል ቦታ በመሄድ ከቀኑ 11፡30 አካባቢ 50 ኤፍዋን የተሰኘ የእጅ ቦምብ ከስምንት የቦምብ ፊዉዝ ጋር ማንነቱ ለጊዜዉ ካልተለየ ግለሰብ በመረከብ ወደ 2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት በመዉሰድ ደብቀዉ ካስቀመጡ በኋላ በነጋታው ከ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ወደ 3ኛ ተከሳሽ ቤት ለመውሰድ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ሰፈራ ተብሎ በሚጣራ አካባቢ በሚገኝ የ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት እያሉ ከነቦምቡ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ሽብርተኛ ድርጅት የመርዳት ሙከራ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ክሱ ለተከሳሾቹ እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ ክሱ እንዲሻሻልላቸው የክስ መቃወሚያ አቅርበው፤ ፍርድ ቤቱ የክስ መቃወሚያውንና የዐቃቤ ሕግ መልስን መርምሮ ክሱ መሻሻል የሚችልበት የህግ አግባብ የለም ሲል የክስ መቃወሚያውን ውድቅ አድርጓል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው፤ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በማረጋገጥ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾችን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል አለመቻላቸው ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

በክስ መዝገቡ ተካቶ የነበረ 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከሉን ገልጾ በነጻ አሰናብቶታል።

ፍርድ ቤቱ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዚያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.