ስታርት አፖችን በተደራጀ ተቋማዊ አሰራር ለመደገፍ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን በተደራጀ ተቋማዊ አሰራር ለመደገፍ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተገለጸ።
የስታርት አፕ ኢትዮጵያ ፎረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።
በመድረኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች (ስታርት አፖች) ተሳትፈዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል÷ስታራት አፖች በርካታ የአሰራር ማነቆዎች ይገጥሟቸው እንደነበር ተናግረው መንግስት ይህን ታሳቢ በማድረግ አዳዲስ የፖሊሲና ህግ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለይ የሚገጥሟቸውን የፋይናንስ ማነቆዎች ለመቅረፍ በስራ ሂደት የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ መቶ በመቶ ለራሳቸው እንዲጠቀሙ ተወስኗል ነው ያሉት።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ መንግስት ስታርት አፖችን በኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ አይተኬ ሚና እንዳላቸው በሚገባ የተገነዘበ የአሰራር ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለስታርት አፖች የሚሆን ግልጽ የፖሊሲ እና የፋይናንስ ድጋፋ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ጠቅሰው÷ይህ ለዘርፉ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ÷ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዲጂታል ዘርፍ ላይ በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ አቅም ያላቸው ወጣቶች መኖራቸውን ገልጸው÷ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ከኢትዮጵያ ባለፈ የዓለምን ችግር የሚፈቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
ስታርት አፕ እና ካፒታል ገበያ ከፍተኛ ትስስር እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ስታርት አፖችን የሚያበረታታ እና ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፖሊሲው ብዙ ህልም ላላቸው ስታርት አፖች ትልቅ የምስራች ይዞ የመጣ መሆኑንም በመድረኩ ተገልጿል፡፡