Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የግሎባል ፐብሊክ ሴኩሪቲ ትብብር ፎረም የቦርድ አመራሮች ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና ናንቶንግ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው “የግሎባል ፐብሊክ ሴኩሪቲ” ትብብር ፎረም የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ነው።

በስብሰባው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ፎረሙ ዓመታዊ የስራ ክንውን ሪፖርት ላይ እንደሚወያይ፣ የግሎባል ሴኩሪቲ ኢንዴክስ ላይ ስለሚደረገው ጥናት ሂደትና የፎረሙ የ2024 ኮንፈረስ ዝግጅትን ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተጠቁሟል፡፡

ፎረሙ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የህዝብ ደኅንነት ላይ በማተኮር የኢትዮጵያን የሕግ አስከባሪ ተቋማትን በማስተባበር ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዘጠኝ ሀገራት የተውጣጡ ከፍተኛ የቦርድ ዳይሬክተሮች በሚመራው ፎረም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አንዱ የቦርድ አባል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ÷ ከጉባኤው ጎን ለጎን በቻይና የሚገኙ ተቋማትን እንደጎበኙ የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም በጃንሱ ግዛት የሚገኘው ሞተር ሳይክል አምራች ሲ ኤፍ ሞተርን የጎበኙ ሲሆን÷ ኩባንያው ለፌደራል ፖሊስ በድጋፍ ለሰጣቸው ዘመናዊ ሞተር ሳይክሎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢያደርግ በኢትዮጵያ እና በቀጠናው ካለው ገበያ ተጠቃሚ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የኩባንያው አመራሮች÷ ለኢትዮጵያ ፖሊስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠው፤ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የመክፈት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከቺንጃን ፖሊስ ኮሌጅ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት የትምህርት እድል አግኝተው እየሰለጠኑ ላሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ኮሌጁ ለሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል አመስግነዋል፡፡

ኮሌጁ ያለውን የረጅም ጊዜ ልምድ እና ተሞክሮ በማካፈል ድጋፍ እንዲያደርግም ለአመራሮቹ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የኮሌጁ አመራሮችም ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ፣ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር እንደሚሰሩና በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.