አዲስ አበባችን ማንንም የማትገፋ የሁላችን መዲና ናት – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባችን ማንንም የማትገፋ የሁላችን መዲና ናት ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ በኮሪደር ልማትና በመልሶ ማልማት የተነሱ ነዋሪዎችን አዲስ በገቡባቸው የመኖሪያ ቤቶች የበዓል አስቤዛ ይዘን በመገኘት ጎብኝተናቸዋል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በተተካላቸው መኖሪያ ቤቶች ማህበራዊ ትስስራቸውን ጠብቀው ሳይበታተኑ ተመሳሳይ የመኖሪያ አካባቢ እና ብሎክ ላይ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
ነዋሪዎቹ የተሻለ የኑሮ ዘይቤ፣ የተሟላ የመኖሪያ ቤት፣ ንጹህ ውሃ፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያ እንዲሁም ለልጆች መጫወቻ ቦታዎችን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ነግረውናልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የመብራት መቆራረጥና ሌሎች ነገሮች በአስቸኳይ እንዲስተካከሉ ነዋሪዎቹ መጠየቃቸውን ገልጸው፤ ለነዋሪዎቹ የተሻለ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር የጀመርነውን ስራ በፍጥነት እናጠናቅቃለንም ነው ያሉት፡፡
አዲስ አበባችን ማንንም የማትገፋ የሁላችን መዲና ናት ያሉት ከንቲባዋ÷ቃላችንን በተግባር መንዝረን አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ፣ ውብና ምቹ፣ ማኅበራዊ ፍትህ የነገሰባት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ለማድረግ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡