Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በምስራቅ ወለጋ ዞን የልማት ሥራዎችን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል መንግስትና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በምስራቅ ወለጋ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ታካልኝ (ዶ/ር) የተመራው ቡድን በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ ኡኬ ከተማ የልማት ሥራዎችንና በግንባታ ላይ ያለውን የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ፣

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንዲሁም የምስራቅ ወለጋ ዞን እና የነቀምቴ ከተማ አመራሮች ተገኝተዋል።

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ በአካባቢው እየተከናወነ ባለ የሰላም ማስከበር ሥራ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል።

በተለይ በዞኖቹ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩና የተቋረጡ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳለጥ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

በነበረው የሰላም እጦት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 57 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስና የእህል ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።

አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው÷በተለያዩ የወለጋ ዞኖች በተደረገ ጉብኝት ህብረተሰቡ ለሰላምና ልማት ያለው ቁርጠኝነት አረጋግጧል ብለዋል።

መንግስትም ይህንን በመገንዘብ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ወደ ስራ መግባቱን ነው የገለጹት።

በዚህም የህዝብ የልማት ፍላጎት ላይ ያተኮሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥ በዞኖቹ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት ይሰራል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.