የጤናው ዘርፍ የተቀናጀ የጋራ ስብሰባ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር የጤናው ዘርፍ የተቀናጀ የጋራ ስብሰባ በመቀሌ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
በመድረኩም የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት እቅድ አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን፤ የባለፈው ስብሰባ ላይ የተቀመጡ የትግበራ ነጥቦች ያሉበት ደረጃ እና የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ መድረኩ በትግራይ ክልል መካሄዱ ጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና ተጠሪ ተቋማት በጋራ በመሆን ለክልሉ ያላቸዉን አጋርነት ለማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል።
በግማሽ ዓመቱ የነበረው ሁኔታ መለስ ብሎ ለመመልከት እና ስራዎችን ለማሻሻል በሚጠቅሙ ነጥቦች ላይ ውይይት ለማድረግ መድረኩ መካሄዱን ገልጸዋል።
አጀንዳዎችን ወደ ተግባር የምናወርድበት እና የአመራር ቁርጠኝነት የምናሳይበት መድረክ ይሆናልም ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አማኑኤል ሀይለ በበኩላቸው፤ የጋራ መድረኩ በትግራይ ክልል እንዲካሄድ መደረጉ ትልቅ ሞራል የሚሠጥ ነው ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ ያለው ግንኙነት ተቀራርቦ ለመስራት በእጅጉ የሚረዳ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ተቀናጅቶ መስራት በሚፈልገው የጤና ስራ ተቀራርቦ በመስራት ዉጤት ማግኘት እንደሚቻል በክልሉ እየታየ ያለዉ የጤና አገልግሎት መሻሻል ምሳሌ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በግማሽ ዓመቱ ክልሎች ያሉበትን ደረጃ እና በየክልሎቹ የተከናወኑ አበይት ተግባራት ላይ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ገለጻ መስጠታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።