Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች ነው – ጠ /ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በናይሮቢ ኬንያ በተካሄደው የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ጉባዔ (አይ ዲ ኤ) ላይ ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው÷ የአፍሪካ ቀንድ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚከሰቱ የተለያዩ አደጋዎች ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እነዚህን ስጋቶች ለመቀነስ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራች መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኢትዮጵያ ደንን መልሶ ማልማት፣ የአረንጓዴ ልማትን ማጠናከር፣ የአካባቢ ልማት ጥበቃን ማጎልበት ላይ አተኩራ እየከወነች ነው ብለዋል።

ለኑሮ የሚመች አካባቢን መፍጠር የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመግለፅ÷ ምቹ የኑሮ አካባቢን ለመፍጠር ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተጨማሪም መንግስት ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በዚህም በሀገሪቱ የስራ እድል ፈጠራን ለማበረታትና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እውን ለማድረግ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝምና በሌሎች የልማት ዘርፎች የ10 ዓመት የልማት እቅዶች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በትምህርት፣ በዲጂታላይዜሽን እና በሃይል አቅርቦት ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ የለውጥ ስራዎችንና ውጤቶችን ለአብነት ማንሳታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

በቀጣናው ለእርቅና ለምክክር ቅድሚያ በመስጠት መሰራት እንዳለበት አፅንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ እርቅና ምክክር እውን እንዲሆን ያከናወናቸው ተግባራትንም ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.