Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር የሙስና ወንጀል ለተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በስር ፍ/ቤት የተሰጠ ዋስትና ፀና

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራንስፖርት ስምሪትና የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር ሙስና ወንጀል ለተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በስር ፍ/ቤት የተሰጠውን ዋስትና አፀና።

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ከሀገር እንዳይወጡ እግድ እንዲጣል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪዎቹ የቀድሞ የህዝብ ትራንስፖርት የተሽከርካሪ ዘርፍ ኃላፊና የትራንስፖር ሎጂስቲክ ሚኒስትር አማካሪ የነበሩት ከድልማግስት ኢብራሂም፣ የትራንስፖርት ማህበራት አመራርና አባል ታምራት በየነ፣ ጌትነት በየነ እንዲሁም የመናኸሪያ የትራንስፖርት ስምሪት ኃላፊዎች አበበ ወ/መስቀል፣ ሺመት መሸሻ፣ ታምራት ለገሰ፣ ጥበቡ ተፈሪ እና እንግዳ ሽኩር፣ ባርናባስ አለሙ፣ ሙስጠፋ ጀማል እና ይታገሱ ተድላ ይገኙበታል።

መንግስት ህዝብን በትራንስፖርት አገልግሎት ለመደገፍ ባዘጋጀው የድጎማ መርሐ ግብር ላይ በጥቅም በመመሳጠር የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር፣ ለግል ጥቅም በማዋል በመንግስት ከ34 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈጸምና ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ መሆናቸውን ጠቅሶ ፖሊስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ማቅረቡ ይታወሳል።

የስር ፍርድ ቤቱ ከ14 ቀን በፊት በነበረ ቀጠሮ በፖሊስና በተጠርጣሪ ጠበቆች መካከል የተከናወኑ ክርክሮችን እና የፖሊስን ጊዜ ቀጠሮ መዝገብ መርምሮ ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ማስረጃ ሊያጠፉ የሚችሉበት እድል ሊኖር አይችልም የሚለውን ግምት በመያዝ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መፍቀድ ተገቢነት የለውም በማለት ተጠርጣሪዎቹ የ50 ሺህ ብር ዋስ አሲዘው ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዶ ነበር።

መርማሪ ፖሊስ በብይኑ ቅር በመሰኘት በመዝገቡ ላይ ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብሏል።

ፖሊስ በይግባኙ ላይ ቀሪ ምስክሮች፣ ማስረጃዎች እንዲሁም የኦዲት ሪፖርት እንደሚቀሩትና ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቅሶ በስር ፍርድ ቤት የሰጠው ዋስትና ተገቢ አደለም በማለት የይግባኝ አቤቱታ አቅርቧል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ ፖሊስ ቀረኝ ያላቸው የምርመራ ስራዎች ተጠርጣሪዎችን በእስር ሊያቆዩ የሚችሉ ምክንያቶች አይደሉም በማለት በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደው የዋስትና መብት እንዲፀናላቸው ጠይቀዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የግራ ቀኝ ክርክሮችንና የስር ፍርድ ቤት ዋስትና የፈቀደባቸውን ስነ-ስርዓታዊ ምክንያቶችን መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ በስር ፍ/ቤት የተሰጠው ዋስትናን አፅንቶታል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.