Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ስለሺ በቀለ በአጎዋ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) በአጎዋ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ የአሜሪካ የኮንግረስ አባልና በኮንግረሱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ አባል ሺላ ቼርፊለስ-ማኮርሚክ ጋር ኢትዮጵያን ከአጎዋ ማግለሉ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስን አስመልክተው መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡

ሲያብራሩም አጎዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባሉ ዜጎች ላይ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በአሜሪካ ባለሃብቶች ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነም አስገንዝበዋል አምባሳደሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እየታዩ ያሉ ግጭቶች፣ የአንዳንድ ቡድኖች ስርዓት አልበኝነት በኢትዮጵያ መረጋጋት ላይ እና እድገት ላይ ተጽዕኖው እያሳደረ መሆኑንም ለለኮንግረስ አባሏ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከኮንግረስ አባል አሚ በራ ጋር አምባሳደሩ ባደረጉት ውይይት የሽግግር የፍትህ ፖሊሲን ማፅደቅ፣ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙና ለስደተኞች የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ፣ ስለአጎዋ ለኢትዮጵያና አሜሪካ የንግድ ግንኙነት አስፈላጊነት፣ የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ወዘተን ጨምሮ የሰላም ስምምነትን ተግባራዊነት ዙሪያ መክረዋል፡፡

በሌላ በኩል አምባሳደሩ ከኮንግረስ አባል ጆን ጋራመንዲ ጋር ባደረጉት ውይይት በአጎዋ፣ በኢትዮጵያ ሊፈጠር የሚችለው አጋርነት እና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የሰብአዊ ድጋፍ እና የምግብ አቅርቦት፣ የሰላም ስምምነት አተገባበር፣ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ስለሚታዩ ግጭቶች ተወያይተናል ብለዋል፡፡

ጆን ጋራመንዲ እና ባለቤታቸው ፓትሪሺያ ከፈረንጆቹ 1966 እስከ 1968 በኢትዮጵያ የሰላም ጓድ ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ሀገሪቱን በተደጋጋሚ ይጎበኙ እንደነበርም ነው ያነሱት።

ጥንዶቹ ችግሮችንና እድሎች ጨምሮ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ማህበረሰብ እና ባህል ጥልቅ ግንዛቤ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.