Fana: At a Speed of Life!

ለትንሳኤ በዓል ወደ ሀገር ለሚገቡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው

ለትንሳኤ በዓል ወደ ሀገር ለሚገቡ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለትንሳኤ በዓል ወደ ሀገር እየገቡ ለሚገኙ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል እየተደረገ ነው::

በአቀባበል ሥነ -ስርዓቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

“ባክ ቱ ዩር ኦሪጂንስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ ለሚኖሩ የ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡት ጥሪ በሶስት ዙሮች እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡

በዚህም ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በመጀመሪያው ዙር ከብዝሃ ባህል መሰረትዎ ጋር ይገናኙ በሚል በተሰየመው መርሐ ግብር ወደ ሀገራቸው ገብተው እንደነበር ይታወሳል።

አሁን ደግሞ ታሪካዊ መሰረትዎን ይወቁ በሚል በተሰየመው መርሐ ግብር 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በ2ኛ ዙር ወደ ሀገር እየገቡ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

በ2ኛው ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው የሀገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ፣ የአያቶቻቸውን እና ቅድመ አያቶቻቸውን አይበገሬነትና መስዋዕትነት እንዲገነዘቡ ያስችላል ተብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከራሳቸው አልፎ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንዲረዱ በማድረግ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው እንዲዳብር ብሎም በዚህ አኩሪ ታሪክ ተነሳስተው በዘመናቸው ፍሬያማ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬት፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች የዋጋ ቅናሽ በማድረግ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያኑን ተቀብለው በማስተናገድ ላይ መሆናቸውንም የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.