Fana: At a Speed of Life!

የስቅለትና የትንሳዔ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የስቅለትና የትንሳዔ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ ለማስቻል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ በአዲስ አበባ ፖሊስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መላው የፀጥታ አካላቱን ያሳተፈ ውይይት ተከናውኗል፡፡

በመድረኩ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታንና መደበኛ የወንጀል መከላከል የተግባር አፈፃፀሞች ላይ ትኩረት ያደረገ ገለፃ የተደረገ ሲሆን÷ ከበዓላቱ መከበር ጋር ተያያዞ በከተማው ላይ እንደ ስጋት የሚታዩ ችግሮችን አስቀድሞ በመለየት በቀጣይ መከናወን በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ በሰጡት መመሪያ÷ በፅንፈኛ ቡድኖች ላይ እየተወሰደ ከሚገኘው ጠንካራ እርምጃ ጎን ለጎን የስቅለትና የትንሳዔ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታ አካላት ቅንጅታቸውን በማጠናከር የክፍለ ከተሞቻቸውን ተጨባጭና ነባራዊን ሁኔታ ያገናዘበ ፀጥታን የማረጋገጥ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዕለተ ስቅለቱ ጀምሮ የፋሲካ በዓልን ተከትሎ በሚመጡ የበዓል ሰሞን ሊኖር የሚችለው የሰውና የተሸከርካሪን እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ቅድመ መከላከል ተግባር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው÷በዓሉ በየ ቤቱ የሚከብር እንደመሆኑ መጠን እንቅስቃሴዎች ከበዓል በፊት ባሉ ቀናት እንደሚበዙ ጠቁመው በተለያዩ ቦታዎች በባዛሮች፤ በገበያ ቦታዎች ላይ በሚስተዋሉ የበዓል ግብዓቶች ላይ ሰው ሰራሽ የግብዓት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ እናዳይደረግ የከተማ አስተዳደሩ ባቋቋመው ግብረ ሐይል ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በንግድ ስርዓቱ ላይ ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ተግባር በማገዝ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡

የምርት አቅርቦት ላይ እና የቁም ከብት ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር የሚያደርጉ ህገ-ወጥ ደላሎች ላይ ተገቢው ክትትል በማድረግ መቆጣጠር እንደሚገባም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ባልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ የሚደረግ ግብይትን መቆጣጠር ትኩረት እንደሚሰጠው ያብራሩት ሃላፊዋ ለትራፊክ ስጋት የሆነውን የጎዳና ላይ ንግድን ጨምሮ የስርቆት ወንጀል ፤ሀሰተኛ የብር ኖት ዝውውር፤ በምግብ ውስጥ ባዕድ ነገር ቀላቅለው በሚሸጡ አካላት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው÷ የ2016 ዓ.ም የስቅለትና የፋሲካ በዓላት በተመሳሳይ የፀጥታ ሁኔታ በሰላም እንዲያልፍ ቀደም ሲል የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር ጥናት ላይ ያተኮረ የስምሪት አቅጣጫ ተግባራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡

ከወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አኳያ በከተማውዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ፤ በመዝናኛ አካባቢዎች፤ በቤተ እምነቶችና በጥናት በተለዩ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ የጥበቃ ተግባር እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡

በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በምሽት ወደ ቤተ እምነቶቹ ለአምልኮት ሲሄድ ምንም አይነት ስጋት እንዳይፈጠር ጠንካራ የጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ገልፀው÷ ህብረተሰቡም ለሰላሙ ስጋት የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙት ለፀጥታ አካላት ተገቢውን መረጃ በመስጠት ተባባሪ መሆን እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ለመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በዓላቱ የጤና፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

በበዓላቱ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችንና ድንገተኛ አደጋዎችን ከመከላከል አንፃር ጥንቃቄ ከማድረግ ባሻገር አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11 እና በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም ወይም በየአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት በአካል በመቅረብ ጥቆማና መረጃ መስጠት እንደሚቻልም አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.