Fana: At a Speed of Life!

ከ374 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 374 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 391 ነጥብ 34 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 374 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡

አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ43 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር ብልጫ አለው ማለታቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ከተሰበሰበው ውስጥም የሀገር ውስጥ ታክስ ድርሻ 235 ነጥብ 19 ቢሊየን መሆኑን እና ቀሪው 139 ነጥብ 1 ቢሊየን ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ የተገኘ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የገቢ አሰባሰቡ በየዓመቱ እየተሻሻለ ቢመጣም÷ ከመንግሥት የወጪ ፍላጎት፣ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ጥመርታ አንጻር ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ከታክስ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አኳያ ተለዋዋጭ የሆነውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ እንደሚኖርባቸውም ለምክርቤቱ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.