Fana: At a Speed of Life!

በሚቀጥሉት ቀናት ከቀላል እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ላይ ይኖራል ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 30 ቀናት ወቅታዊው ዝናብ ከበልግ አብቃይ የሀገሪቱ ክፍሎች እየቀነሰ ከክረምት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች መጠናከር ጋር ተያይዞ ወደ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ እንደሚስፋፋ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡

በመጪው ወር ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንደሚጠናከሩና ከዚህም ጋር ተያይዞ ከቀደሙት ሶስት የበልግ ወራት በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተሻለ ዝናብ በብዙ የሀገሪቱ ቦታዎች ላይ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ከቀላል እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ላይ እንደሚኖርና በአንዳንድ ሥፍራዎችም ላይ ከባድ ዝናብ የሚዘወተርና አልፎ አልፎ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥለዉ ወር ከኦሮሚያ ክልል የቄለም ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉባቦር፣ ጅማ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፤ አዲስ አበባ፤ ከአማራ ክልል የዋግህምራ ዞኖች፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡

እንዲሁም የአፋር ክልል ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅ፣ የምስራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የሱማሌ ክልል ዞኖች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን÷ በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ።

በተለይም በሰሜን ምስራቅ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ምስራቅ፣ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚኖረው ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ የማስከትል አቅም ሊኖረው ስለሚችል ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.